ከኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ የተመዘገቡ ድሎችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቁ እህትና አጋር ድርጅቶች ገለፁ

የኦህዴድ እህት ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች በ9ኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መልዕክታቸውን ያስተላለፉት መካከል የደኢህዴን፣ የብአዴን፣ ህውኃት እና የአጋር ድርጅት ተወካዮች የኦህዴድ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በርካታ ድሎች በተገኙበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንንም የሚያጠናክሩ ድሎች ከጉባዔው እንደሚጠብቁም አንስተዋል።

የደህዴን ስራ አስፈፃሚ አባል መሠረት መስቀሌ ድርጅታዊ ጉባዔው የሚያስቀምጣቸው ውሳኔዎች የኦህዴድ/ኢህአዴግን እንዲሁም የሀገሪቱን መጪ ዕድል የመወሰን አቅም ያለው መሆኑን በንግግራቸው አንስተዋል።

ደኢህዴን የመፍትሔ አካል ለመሆን ቀደም ብሎ የድርጅቱን የቀድሞ ሊቀመንበር የ
ሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በመቀበል የሥልጣን ሽግግሩ እንዲሳካ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አንስተው፥ በቀጣይም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ማበብ ከእህት ድርጅቱ ኦህዴድ ጋር በጋር እንደሚቆም ገልጸዋል።

በቅርቡ የተጀመረው የይቅርታ፣ የፍቅርና የሰላም ጉዞ መልካም መሆኑን ያነሱት ተወካይዋ፥ ህዝቡ ለመብቱና ለጥቅሙ መከበር በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚገባውም አንስተዋል።

የብአዴን ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ታሪካዊ ጉባዔ መሆኑን አንስተው፥ ሀገሪቱ ከጥፋት በመውጣት ህዝቧ ብሩህ ተስፋ የሰነቀበት ወቅት መሆኑና ወቅቱ የሚወልዳቸው በርካታ ፈተናዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ፈተናውን በተናጠል ሳይሆን በጋር በመረባረብ የተለየ ጊዜ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ተወካዩ አንዳንድ ወገኖች በህዝቦች መካከል በተለይም በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች ላይ የቤት ስራ ለመስጠት እንደሚጣጣሩ አንስተው ይህ እንደማይሳካላቸውም አስታውቀዋል።

በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለፉት ከፍቅርና ከአንድነት ትርክቶች ይልቅ የቂም በቀል ትርክቶች ላይ ያተኮረ ስውር ደባዎች ሲፈጸሙ ይስተዋላል፤ ይህም በሁለቱ ህዝቦች ማርከሻ መድሐኒት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጽንዖት በመስጠት በንግግራቸው አንስተዋል።

በዚህም ምሁራንና ፖለቲከኞች እንዲሁም ሌሎች ይህን ጥቀርሻ ከማጉላት በመጠበቅ “ጸዓዳችን ላይ ያተኮረ ትርክት እንዲመጣ” እንዲሁም ብቸኛው አማራጭ ከጥላቻ በላይ ፍቅር መሆኑን በመጥቀስ ህዝቦችን የሚለያዩ የአስተሳሰብ ግንቦችን ማፍረስ ይገባል ብለዋል።

የኦህዴድ ጥንካሬ የብአዴን ጥንካሬ የኦህዴድ ድክመት የብአዴን ድክመት መሆኑን አንስተው፥ ወቅቱ የወለዳቸውን ፈተናዎች በጋራ መፍትሔ እንደሚሰጡት አንስተዋል።

የህወኃት ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል ዶክተር አብርሃም ተከስተ ደግሞ ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ለሰጠው አመራር ህወኃትና የትግራይ ህዝብ ክብር አለው ብለዋል በንግግራቸው።

ኢህአዴግ ባለፉት ጊዜያት በወሰዳቸው እርምጃዎች መልካም ዕድል መምጣቱን የጠቀሱት ዶክተር አብርሃም ፈተናዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በጉባዔው ሰላምን፣ ዴሞክራሲን እና ሌሎችንም መብቶች የሚያረጋግጥ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

ለህገመንግስታዊ ፌደራላዊ ስርዓት መጎልበት፣ ለልማታዊ መንግስት ግንባታ፣ ለህግ የበላይነት መከበር እና ለሌሎችም ድርጅታቸው በጋራ ከኦህዴድ ጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ሌሎች የአጋር ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)