በቡራዩና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ችግር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፀጥታ አካላትና የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በቡራዩና አካባቢ ተከስቶ በነበረው ችግር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አካላትና የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ፡፡

እንዲሁም ችግሩን ለማረጋጋት በተሰራው ስራ አማካኝነትም ወደ ሰላም መመለሱን ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አንስተዋል፡፡

በግጭቱ ተጎድተው ከነበሩ ሰዎች መካከል በዛሬው ዕለት የሦስት ሰው ህይወት ማለፉን ገልጸው በአጠቃላይ እስከአሁን የሟቾቹ ቁጥር 26 መድረሱን በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

የጸጥታ ኃይል ባደረገው አሰሳም በዛሬው ዕለት ሁለት ክላሽ እና አራት ሽጉጥ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን፥ እስከአሁን አምስት ክላሽ 12 ሽጉጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ገልጸዋል፡፡

በግድያ የተጠረጠሩ 46 ሰዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፀጥታ አካላትና የሥራ ኃላፊዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎችና ቄሮዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቤቶችን ሲያድሱ እና ሲሰሩ መዋላቸውንም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም የተዘረፉና የተሸሸጉ ንብረቶች ለባለንብረቶች እንዲመለሱ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

በዛሬው ዕለትም ከተፈናቃዮቹ የተውጣጡ 50 ግለሰቦች ቡራዩ በመሄድ ከከተማ መስተዳድሩ አመራሮችና እና ከሽማግሌዎች ጋር ወደ ቀያቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ዶክተር ነገሪ ገልጸዋል፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)