በአዲስ አበባ በተከሰተው ግጭት 28 ሰዎች መሞታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 7/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተከሰተው ግጭት 28 ሰዎች መሞታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጄር ጀኔራል ደግፌ በዲ በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግጭቱ የተከሰተው ወጣቶች ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል እና ቀለም ለመቀባት በሚያደርጉት ጥረት ሌላኛው ወገን ከልካይ በመሆኑ የተነሳ ሲሆን ይህ ድርጊት የፖሊስ ስራ በመሆኑ ወጣቱ እርምጃ ሊወስድ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡

 

በግጭቱ ምክንያትም በከተማዋ 28 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሰባቱ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በፀጥታ ኃይሎች ከተገደሉት 7 ሰዎች መካከል አንዱ በስህተት እንደተገደለም ጠቁመዋል፡፡

በግጭቱ ወቅት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰና በተለያዩ ባንኮች ላይ ዘረፋ ለማካሄድ ሙከራ እንደተደረገ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በተከሰተው ሁከት የከተማዋ የንግድ ሥርዓቱ ላይ መስተጓጓል ተፈጥሮ እንደነበረም ተገልጿል፡፡

በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለህግ የማቅረብ ሥራ ተከናውኖ ተጠርጣሪዎች በህግ ጥላ ስር እንደሚገኙ የተናገሩት ኮሚሽነሩ ከተያዙት ውስጥም 1ሺህ 204 የሚሆኑት ለፀባይ ማሻሻያ በጦላይ ማሠልጠና ተቋም እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በህግ መጠየቅ ያለባቸው 174 ተጠርጣሪዎች በአሥር ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከድርጊቱ ጋር ተያይዞ ህገወጥ ንግድ የሚካሄድባቸውን ሺሻ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችንና ቁማር ቤቶችን የማስቆም ስራ እንደተሰራ እና ከነዚህ ቤቶች ውስጥም 1ሺህ 459 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ኮሚሽነር ሜጄር ጀነራል ደግፌ ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጥተው በአዲስ አበባ ውስጥ ድርጊቱን ተገን በማድረግ ዝርፊያ ሊያከናውኑ የነበሩ ቡድኖችም እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ወጣቶችን የከተማው ፖሊስ አፈና እያደረገ ነው በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው ወሬ አግባብ አለመሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በግጭቱ ምክንያት በደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ እንደዚህ አይነት ችግር እንዳይፈጠር በአዲስ አበባ አምስቱም በሮች ክትትል እንደሚያደርግና በከተማዋ ዙሪያ ካሉ ከተሞች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡