ሰዎች ታፈሱ ተብሎ የሚሰራጨው ወሬ የተሳሳተ ነው – አቶ አህመድ ሽዴ

በአዲስ አበባ ከተማ ሰዎች ታፍሰው ተወሰዱ ተብሎ የሚሰራጨው ወሬ የተሳሳተ መሆኑንና ህብረተሰቡን ለማደናገር የሚሰራ ስራ እንደሆነ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ በተለያዩ አካባቢዎች ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች በህጋዊ መንገድ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

መንግስት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከመስከረም 2 ጀምሮ የፖለቲካ ኃይሎችን ለመቀበል በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ያልተገባ ፉክክር ግጭቶች መፈጠራቸውን አስታውሰዋል ።

እየሰፋ በሄደው ግጭትም በቡራዩ 27 ሰዎች በአዲስ አበባ 28 በጥቅሉ የ55 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በቡራዩ ከተማ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እንዳጋጠመና 3 ሺህ 50 ሰዎችም መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ግጭቶች የብሄር ማስመሰልና በማህበራዊና በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ መረጃዎችን በማቅረብ ግጭቱን ለማባባስ እንቅስቃሴ ተደርጓል ብለዋል።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ከግጭቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው 170 ሰዎችና በቡራዩ ከተማ ደግሞ 390 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም በአዲስ አበባ ሁከቱና ብጥብጡን ለማማባባስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ 1 ሺህ 200 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ችግሩን ለመቆጣጠር የፍትህና የፀጥታ አካላት ባደረጉት ርብርብ ችግሩ በቁጥጥር ስር እንደዋለ አስታውቀዋል።                                                                             

መንግስት በደረሰው የህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ሀዘን ሚኒስትሩ ገለፀዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)