ህወሃት በድርጅታዊ ጉባኤው ክልሉንና ሀገሪቱን የሚጠቅም ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተስፋ አለን – ዶ/ር ደብረፅዮን

በህወሃት ድርጅታዊ ጉባኤ የትግራይ ክልል እና ሀገሪቱን የሚጠቅም ውሳኔ እንደሚተላልፍ ተስፋ እንዳላቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል።

13ኛው የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ በመቐለ መካሄድ ጀምሯል።

ድርጅታዊ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፥ 13ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ታሪካዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ጉባኤው የየክልሉ እና የሀገሪቱ ህዝብ ህዳሴ ማረጋገጫ በመሆኑ ጉዟችንን የተለየ ያደርገዋል ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፥ በ13ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉም ጠቅሰዋል።

በ13ኛው የህወሃት ድርጅታዊ ጉባኤ ለትግራይ ክልል እና ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ውሳኔዎች እንደሚተላልፍ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ሊቀመንበሩ።

ድርጅታዊ ጉባኤው ከውሳኔዎቹ በተጨማሪም አዳዳስ አመራሮች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ ለማድረግ ምርጫ እንደሚካሄድም ነው ዶክተር ደብረፅዮን በንግግራቸው ያመላከቱት።

ዶክተር ደብረፅዮን አክለውም ህወሃት በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ድርጅቱ ከምንም በላይ እራሱን እየተፈተሸ ድክመቶቹን ያለ ምህረት እየታጋለ ከነበረበት ችግር በመላቀቅ ለውጦችን ማምጣት የሚችል እንደሆነ ገለፀዋል።

አሁንም ከችግሮች ለመውጣት ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ የመንግስትና የህዝብ መድረኮች በስፋት እንደሚኖሩ ነው ያስታወቁት።

በአሁኑ ወቅትም በገጠርና በከተማ የሚኖረው ህብረተሰብ ከድህነትና ኋላቀርነት በፍጥነት እየተላላቀቀ እንደሚገኝና አኗኗሩም ደረጃ በደረጃ  እየተሻሻለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

እየታገልን ያለንበት ዓላማ ህዝቡን ከድህነት የማላቀቅ ብቻ ሳይሆን  በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ነው በማለት ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ በርካታ ችግሮችን አልፎ  እንደደረስከው ሁሉ አሁን የተጀመሩ ለውጦች ቀጣይነት ወደፊትም ከህወሓት ጎን እንዲቆም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ህውሃት ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ባደረገው ትግል አሁን ያለው ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ  ለውጥን ማስመዝገቡን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ በውጭ እና በአገር ውስጥ ህገ መንግስቱንና መንግስትን ለመናድ እየተደረገ ያለውን ሙከራ እንደሚያወግዙም ዶክተር ደብረፅዮን በንግግራቸው አንስተዋል።

የዜጎች ህገመንግስታዊ መብት እየተጣሰ መጥቷል ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን፥ ብሄርን ከብሄርን የሚያጋጩ  ኃይሎችን ልንመክታቸው ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም የህዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ለደረሰው የዜጎች ሞትና ጉዳት የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን ሲሉም ዶክተር ደብረፅዮን አስታውቀዋል።

የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት በተመለከተ፥ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ያለፈውን የችግር ግዜ ለመካስ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም ገልፀዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)