አሁን የተፈጠረውን የለውጥ ፍላጎት መሸከም የሚችል አመራር ወደፊት ማምጣት ግድ ይለናል-ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

በ10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ድርጅቱ በክልል እና በሀገር ደረጃ የተፈጠረውን የለውጥ ፍላጎት መሸከም የሚችል አመራር ወደፊት ለማምጣት የግድ የሚለን ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪያት።

ወይዘሮ ሙፈሪያት 10ኛውን የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባዔ በዛሬው በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ 10ኛው የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባዔ እንደ ሀገር እና እንደ ክልል አዳዲስ ለውጦች እየተካሄደ ባለበት ወቅት በመካሄዱ ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።

ጉባዔው እንደ ሀገር እና እንደ ክልል የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ህዝቡ ከለውጡ እያገኘ የመጣውን ተስፋ ከፍ ለማድረግ በጋራ መስራት እና አቋም መያዝ ባለንበት ወቅት የሚካሄድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ደኢህዴን ባለፉት 26 ዓመታት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በሰራቸው ስራዎች ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም በርካታ ድሎቸን ማስመዝገብ የቻለ ደርጅት ነውም ብለዋል።

ድርጅቱ በክልሉ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎቸን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ የመጣ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ ሆኖም ግን የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነው የክልሉ ህዝብ የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን የቆየባቸው ጊዜያቶች እንደነበሩም አውስተዋል።

ድርጅቱ ባለፉት 26 ዓመታት ለሀገር አንድነት ተምሳሌት በሚሆን መልኩ 56 ብሄሮችን በማስተባበር ህብረ ብሄራዊነትን በተግባር ማሳየቱንም ሊቀ መንበሯ አንስተዋል።

ድርጅቱ እስካሁን በርካታ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም፥ አሁን ፈታኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ በመሆናችን እና ወደ ፊት በርካታ ስራዎች ስለሚጠበቅብን ተግተን እንዲንሰራ በምንገደድበት ወቅት ላይ ደርሰናል ሲሉም ተናግረዋል።

ደኢህዴን የክልሉን ህዝብ በማስተባበር በርካታ ድሎቸን እያስመዘገበ የመጣ ድርጅት ቢሆንም በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውታል ያሉት ሊቀ መንበሯ፥ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በብስለትና በጽናት በማለፍ ለሀገሪቱ ልማት የበኩሉን ማበርከቱንም ገልፀዋል።

ጉባዔው በአሁኑ ወቅት በክልሉ እና በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ አነቅስቃሴዎችን የሚመጥን አዲስ የለውጥ አመራር እንደሚያደራጅ እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ድርጅታዊ ጉባዔው ወደ ቀጣይ የድል ምእራፍ የምንሸጋገርበት በመሆኑ ለህዝብ ልብ ቀረብ የምንልበትን ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች እንደሚተላለፉበት አምነት አለኝም ብለዋል።

በዚህም ጉባዔው በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ፣ የወጣቶችና የሴቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎቸን የሚያስቀጥሉ አቅጣጫዎቸን እንደሚያስቀምጥ አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከድርጅቱ አላማና ያፈነገጡ፣ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ሴራዎች እየተስተዋሉ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ ይህንን ሁኔታ በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት የህግን የበላይነት ለማረጋገጥ በአንድነት መስራት ግድ ይለናል ሲሉም ተናግረዋል።