ፍርድ ቤቱ አቶ አብዲ መሃመድ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ጨምሮ በአራት ተጠርጣዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡

የፌደራል መርማሪ ፖሊስ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ የ18 ሟቾችን እና የ438 አካል የደረሰባቸውን ግለሰቦች የህክምና ማስረጃ መሰብሰቡንና ዘጠኝ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ለችሎቱ አብራርቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ወንጀል ችሎት የመርማሪ ፖሊስ የተሰጠው ጊዜ የሰራቸው ስራዎች እና ቀሩኝ ያላቸው ምርመራዎች እንዲሁም የተጠርጣሪዎችን አስተያየት አዳምጧል፡፡

በዚህም መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ የደረሰበትን የጉዳት መጠን ማሰባሰቡን፣ ወደ ጎረቤት ሀገር የተወሰዱ በርካታ ተሸከርካሪዎችን ከሀገራቱ ጋር ተነጋግሮ ማስመለሱን፣ በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ልማት ባንክ የደረሰውን የዝርፊያ መጠን ሰነድ ማሰባሰቡን፣ በርካታ ለወንጀሉ መጠቀሚያ ውሎ የነበረ ገንዘብ መረከቡን፣ በክልሉ ሴቶች ላይ የመደፈር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሴቶች ላይ የህክምና ማስረጃ መሰብሰቡን፣ የ41 ግለሰቦች የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ አብራርቷል፡፡

እንዲሁም ቀሪ ያለውንም የተደፈሩ ሴቶች ቀርበው እንዲያስረዱ ማድረግ፣ ቀሪ ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበል፣ የኤጎ ቡድን ይዞ የተሰወረውን መሳሪያ ማስመለስ የሟቾችን አስከሬን ምርመራ ማስራትና የተያዙ ሞባይሎችን ላፕቶፖችን ማስመርመር በወንጀሉ የተሳተፉ በጎረቤት ሀገር የተደበቁትን መያዝ ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን ወደ አማርኛ መመለስ ስራ እንደሚቀረው አብራርቶ ለዚህም ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

አቶ አብዲ በበኩላቸው የጨጓራ እና የደም ግፊት ህክምና እንዲደረግ ፍርድ ቤቱ ያዘዘ ቢሆንም እስከአሁን ግን እንዳልታከሙ ገልጸዋል፡፡

የታሰሩበት ቤትም ጨለማ ቤት እንደሆነና የፀሐይ ብርሃን እንደማያገኙ በሶማልኛ ቋንቋ ብቻ መግባባት ከሚችሉ እናታቸው ጋር በአማርኛ ካልሆነ በሌላ ቋንቋ መነጋገር አይቻልም ተብለው ሳይገናኙ መመለሳቸውን በመጠቆም በተመሳሳይ ከባለቤታቸው ጋር በሶማልኛ ሰላምታ በመለዋወጣቸው ምክንያት አንድ ቀን መቀጣታቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የቀድሞ የሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኋላፊ ወይዘሮ ራህማ አህመድ በበኩላቸው በሴት ጠባቂ ድብደባ እንደደረሰባቸው በመናገር ከለላ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይም ሌሎች ተጠርጣሪዎች በታሰሩበት ቦታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸምባቸው አስታውቀዋል፡፡

ፖሊስ በበኩሉ ሰኞ ዕለት በሚደረገው ጉብኝት የህክምናውንም ሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ያለመናገራቸውን እንዲሁም ችግር  አለባችሁ ተብለው ሲጠየቁ ችግር ያለመኖሩን መግለጻቸውን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም  የህክምና ባለሙያዎች ህክምና እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ እንዳደረሱም ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በተቃራኒው በተጠርጣሪዎች ስድብና ዛቻ እንደሚደርስበትም ለፍርድቤቱ ገልጿል፡፡

የክልሉ የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር ፈሪሃን ጣሂርን በተመለከተ በክልሉ በየፖሊስ ጣቢያው የታሰሩ እስረኞችን ሰዋራ ቦታ ወስደው እንዲገደሉ ማድረጋቸውን ማስረጃ አለኝ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ በሳቸው በኩል ሲሰጥ እንደነበረ አረጋግጫለው እሳቸው የሰጡትን ዘጠኝ የጦር መሳሪያዎችን አስመልሻለው ሲል ገልጿል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤትም ፖሊስ በተናጠልና በዝርዝር ተሳትፏቸውን እንዲያቀርቡተጨማሪ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ አያያዝን በተመለከተም ክትትል እንዲደረግ አዟል፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)