የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ከማይክ ፖምፒዎ ጋር ተወያዩ

ኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ አቻቸው ማይክ ፓምፒዎ ጋር በሁለትዮሽና የጋራ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ።

ሚኒስትሮቹ በቆይታቸ፥ በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊና ሀገራቱ በሚጋሯቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ነው ተገለፀው።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኢትዮጵያ መንግስት ወሳኝና ዘርፈ ብዙ ለውጦችን እያካሄደ መሆኑን በውይይታቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡

ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማትን መገንባትም የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸው አሜሪካ ይህን ሂደት እንድታግዝ ጠይቀዋል፡፡

የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያሉትን የቢዝነስ እድሎች እንዲጠቀሙም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።

ማይክ ፖምፒዎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ስራዎችን አድንቀው አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል ፡፡
ሚኒስትሮቹ በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲረጋገጥ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል ፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ከኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳሌህ ና ከጅቡቲ አቻቸው መሀመድ አሊ የሱፍ ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ቆይታቸው ከድርጀቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒቶ ጉቴሬዝ ጋር በኒው ዮርክ መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እየታዩ ባሉ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ዙሪያ እና ቀጣይ ፈተና የሚሆኑ ጉዳዮችን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለው ላይ ተወያይተዋል።

እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ጉባዔ ጎን ለጎን ከቤልጅየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲዲየር ራይንደርስ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል ፡፡

ራይንደርስ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላምና ወዳጅነት ሂደትን እንዲሁም በቀጠናው የሚታየውን አዲስ የሰላምና ሁለገብ የትብብር ምዕራፍ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)