በትግራይ ክልል ዴሞክራሲን ማስፈንና ልማትን ማረጋገጥ የአዲሱ አመራር ትኩረት ይሆናል – ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመቀሌ ሲካሄድ የቆየው 13ኛ የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሃት/  ድርጅታዊ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ተጠናቋል።

ጉባኤውን በንግግር የዘጉት የድርጅቱ ሊቀመንበር በመሆን ዛሬ በድጋሚ የተመረጡት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አዲሱ አመራር ለትግራይ ክልሉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለክልሉ የዴሞክራሲ እና የልማት ጥያቄ መመለስ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

ጉባኤው ዴሞክራሲያዊ ትግል የተደረገበት የለወጥ እና ታሪካዊ እንደነበር አንስተዋል።

ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር አዲሱ አመራር ቀን ከሌት እንደሚሰራ አረጋግጣለሁ ያሉት ሊቀመንበሩ ፥ የጉባኤውን ውሳኔዎች ወደሚበላ እና ሚጠጣ ለመቀየር ሁላችንም መረባረብ አለብን ብለዋል።

በትግራይ ክልል ዴሞክራሲን ማስፈንና ልማትን ማረጋገጥ የአዲሱ አመራር ትኩረት እንደሚሆንም ነው የገለፁት።

ህገመንግስታዊ የፌደራል ስርዓቱን ለመጠበቅ ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ እንሰራለንም ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ከተሳተፉ ነባር አመራሮች መካከል አምባሳደር ስዩም መስፍን በሰጡት አስተያየት፥ ጉባኤው ሰፊ ትግል የተደረገበት፣ ምሁራን በስፋት የተሳተፉበት እና ግልፅ ክርክርና ውይይት የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል።

የህወሃት ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ ከመጠናቀቁ በፊት 55 የድርጅቱን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር መርጧል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)