የ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔን ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከዛሬ  ጀምሮ  ለማካሄድ ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ።  

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ፥ በነገው ዕለት በሓዋሳ ከተማ የሚጀመረው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ አስፈላጊ ዝግጅቶች በሙሉ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ለ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የሎጂስቲክ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ጉባዔተኞች እና ተጋባዥ እንግዶች ሀዋሳ ከተማ እየገቡ መሆኑንም ነው አቶ ፍቃዱ ያስታወቁት።

አቶ ፍቃዱ አክለውም ፥ በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይም ለውጡን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል ብለዋል።

እንዲሁም ጉባዔው በመቐለ ከተማ በተካሄደው 10ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና የተላለፉ ውሳኔዎች አፈፃፀመን እንደሚገመግምም አስታውቀዋል።

በጉባዔው ላይ 2 ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ያሉት አቶ ፍቃዱ፥ ከእነዚህ ውስጥ ከአራቱም እህት ድርጅቶች 1 ሺህ ሰዎች በድምፅ እንደሚሳተፉም ገልፀዋል።

በተጨማሪም የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጋባዥ የውጭ ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ 1 ሺህ ሰዎች ይሳተፉበታል።(ኤፍቢሲ)