የሲአን አመራሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገቡ

ከ18 ዓመታት በላይ በተለያዩ አገሮች ሲንቀሳቀስ የነበረው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አመራሮች ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

የንቅናቄው አመራሮች ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ያቀረቡት ጥሪ በመከተልና በሀገሪቱ ውስጥ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ በማየት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተናል ብለዋል፡፡

የንቅናቄው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደምቦዋ ከአ እንደተናገሩት በቀጣይ በተናጠል ወይም በጋራ እንዴት መስራት እንዳለበት ንቅናቄው ከወሰነ በኋላ ወደ ስራ ይገባል፡፡

በተፈጠረው እድል ህጋዊ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ፓርቲው ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ከአሁኑ የለውጥ አመራር ጎን በመሆን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በትጋት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው ንቅናቄው በሰላማዊ መንገድ ለመቀሳቅስ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባቱ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርግ ገልጸው፣ በቀጣይ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዴሞክራሲ የበለጠ እንዲሰፋ ፓርቲያቸው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡