በቤኒሻንጉልና ደቡብ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ኮሚሽኑ ጠየቀ

በካማሺ፣ ሸካና ከፋ ዞኖች የተከሰቱት ግጭቶች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ኮሚሽኑ ጠየቀ። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከማሺ ዞን እና በደቡብ ክልል ሸካና ከፋ ዞኖች የተከሰቱት ግጭቶች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው አስቀድሞ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ከሃዋሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በእነዚህ ቦታዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እና ግጭቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ላይ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የገለፁት።

በእነዚህ ሶስት ዞኖች የዜጎች የመንቀሳቀስ እና ንብረት የማፍራት መብት መገደቡን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ወደ ሶስቱም አካባቢዎች መርማሪዎችን ቢልክም ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን እና መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት።

የፀጥታ አካላትም ግጭቶቹን ለማስቆም ተገቢውን እርምጃ እየወሰዱ አለመሆናቸውን ከአካባቢዎቹ መርማሪዎች ለኮሚሽኑ በስልክ ያደረሱት መረጃ እንደሚጠቁምም ገልፀዋል።

አሁን ላይ በይፋ በግጭቶቹ የሞቱ እና የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርንም በዚህ ምክንያት በአግባቡ ማጣራት አለመቻሉን በማንሳት ይህም የችግሩን ስፋት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ችግሩ በተፈጠረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ገብቶ የማረጋጋት ፣ ህግ እና ስርዓትን እንዲሁም የዜጎችን መብት የማስከበር ስራ እንዲያከናውን ነው የጠየቁት።

እስካሁን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ግጭት ካለባቸው አምስት ወረዳዎች መካከል በሁለቱ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመግባቱ የተሻለ ሁኔታ እየታየ መሆኑን ዶክተር አዲሱ አስታውቀዋል።

በእነዚህ መከላከያ በገባባቸው ቦታዎችም ኮሚሽኑ ከነገ ጀምሮ ምርመራ እንደሚጀመር ነው ያስታወቁት። ምርመራውንም በኃላፊነት መንፈስ ያከናውናል ብለዋል።

ዶክተር አዲሱ በመግለጫቸው በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከልና ሲከሰቱም በዘላቂነት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ጥናት ኮሚሽኑ አድርጎ ለመንግስት ማቅረቡን አስታውቀዋል።(ኤፍቢሲ)