በቀጣይ ሁለት ዓመታት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ከህዝብ ጋር በመሆን በትኩረት ይሠራል -ዶክተር አብይ

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የተጀመሩ  የልማት ሥራዎችን ለማከናወን  ከኢትዮጵያ  ህዝብ  ጋር   በመሆን በትኩረት  ለመሥራት በኢህአዴግ ጉባኤ  መወሰኑን  የኢህአዴግ  ሊቀመበር ዶክተር አብይ  ተናገሩ ።

ዶክተር አብይ በዛሬው ዕለት የደቡብ ክልልና የሲዳማ ሽማግሌዎች 11ኛው  የኢህአዴግ ጉባኤ  መጠናቀቅን በተመለከተ  በሐዋሳ ስታዲየም  በተዘጋጀው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኘተው ንግግር አድርገዋል ።

ዶክተር አብይ በንግግራቸው ምርጫው እስኪካሄድ ድረሰ  ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን  በግብርና ፣ በመስኖ ልማት፣ በኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና በመሳብ  የወጣቶች  የሥራ አጥነትን  ችግር ለመቅረፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት  ለመሥረት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል  ። 

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከሁሉ በላይ ሰላም ፣ ልማት ዴሞክራሲና  እኩልነት በመሆኑ በእውነት  የተመሠረተ ሥራ  የሁሉንም ጥቅም ባማከለ ሁኔታ  የሚሠራበት ጊዜ  እንደሚሆን  ጠቁመዋል ።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን  የአገሪቱን የባህልና ታሪክ እሴቶቻች እንዲያውቁ ለማድረግ  ሰላምን  በማስጠበቅ  በቱሪዝም  ዘርፍ  ተገቢውነ ሥራዎች  ለማከናወን  እንደሚገባ   ዶክተር አብይ ተናግረዋል ።

ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባን ይበልጥ ውብና የፀዳች ከተማ ለማድረግም የአዲስ አበባ   ወጣቶችን  በማስተባበር  ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ  ኢህአዴግ  በልዩ ትኩረት ከሚሠራቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ዶክተር አብይ አመልክተዋል ።

ኢህአዴግ ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበት ድርጅትና የራሱን አንድነት ከመጠበቅ ባሻገር የኢትዮጵያውያንን አንድነት ጠብቆ የሚጓዝ ድርጅት በመሆን ለሕዝብ ተገቢውን  አገልግሎት የሚሠጥ እንደሚሆን ከውዲሁ  ቃል እንደሚገቡ  ዶክተር  አብይ በሀዋሳ ስታዲየም ለተገኘው  ህዝብ ተናግረዋል።

በተቋማት የሚታዩ  ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ ለህዝቡ  ተገቢውን መልካም አስተዳደርና ተጠያቂነትን ለማስፈንም በድርጅታቸውን ትኩረት ተሠጥቶት ልዩ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ሥራዎች  እንደሚካሄዱ ዶክተር  አብይ በንግግራቸው ጠቅሰዋል ።

በመጨረሻም ሁሉም ዜጋ  አባቶች ላስረከቡን አገር በሰላም ፣ በልማት ፣ ለብልጽግናና አገሪቱ ዕድገት  ሁሉም ጸሎት እንዲያደርግም ዶክተር አብይ  ለህዝቡ ጥሪ አድርገዋል ።