ጨፌ ኦሮሚያ 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

የጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ አመት 5ኛ የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።

ስብሰባው የክልሉን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀትና ስልጣንና ሃላፊነታቸውን ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለማጽደቅ ነው ተብሏል።

ረቂቅ አዋጁ ችግር የሚስተዋልበትን የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት፣ የሰው ሃይልና በጀት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋለውን ሰፊ ክፍተት ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም በቢሮ ደረጃ ተከማችተው የሚገኙ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀቶች ታች ካለው ማህበረሰብ ጋር ቀርበው እንዲያገለግሉ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋልም ነው የተባለው።

ጨፌው ከዚህ ባለፈም የክልሉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።

በተጨማሪም በቁጥር 61/1994 የወጣውን የሰራተኞች አዋጅ ለማሻሻል በወጣው ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ማፅደቅም በጨፌው ስብሰባ ከመሚጠበቁት ውስጥ ነው። (ኤፍ.ቢ.ሲ)