በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች 82ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

በቤኒሻንጉልና ጉምዝና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች 82ሺህ የሚሆኑ ዜጎች  መፈናቀላቸውን  የምስራቅ ወለጋ ዞን  አስተዳደር አስታወቀ ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ ለዋልታ እንደገለጹት በቤኒሻንጉል ክልል ከካማሺ ዞን እንዲሁም በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች  82ሺህ የሚሆኑ  ዜጎች ተፈናቅለው  በኦሮሚያ ክልል በዘጠኝ መጠሊያ ጣቢያዎች ተጠልለው ድጋፍ  እየተደረገላቸው  ይገኛሉ ብለዋል ።

በኦሮሚያ ክልል ተጠልለው  የሚገኙት ተፈናቃዮች በፌደራል መንግሥት ፣በክልል መንግሥት ፣በነቀምት አካባቢ ህብረተሰብ  አስፈላጊው  ድጋፍ  እየተደረገላቸው መሆኑም አቶ ብርሃኑ  ተናግረዋል ።

ዋልታ ያነጋገራቸው ነፈናቃዮች እንደተናገሩት የነቀምቴ ከተማ አካባቢ ነዋሪ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝና መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሠጣቸውም ጠይቀዋል ። 

እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ  ከተከሰተው ግጭት ምክንያት ከተፈናቀሉ  ዜጎች መካከል  20 ሺህ የሚሆኑትን  ወደ  ነበሩበት  ቀዬ  ለመመለስ  ተችሏል ።

በቀጣይም ሌሎችን ተፈናቃዮችን ወደ  ቀያቸው ለመመለስና መልሶ  ለሟቋቋም የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ጋር በጋራ  እየሠራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል ።

በተያያዘ ዜናም የአማራ  ብሔራዊ ክልል በቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው  በምስራቅ ወለጋ ዞን በነቀምቴ ከተማ ተጠልለው  ለሚገኙ  ተፈናቃዮች የ200 ኩንታል ሩዝና የ200 ኩንታል  ማኮረኒ ድጋፍ  አድርጓል  ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው የአማራ  ብሔራዊ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተፈናቃዮችን ከጎበኙ በኋላ ችግሩን  በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው የሁለቱም ክልል አመራሮች ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠሩ መነጋገራቸውን ገልጸዋል ።

በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ  ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች ከተፈናቀሉት አጠቃላይ 82ሺህ ዜጎች መካከል 16ሺህ የሚሆኑት የአማራ  ክልል ተወላጆች ናቸው ።