ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የደምህት ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገቡ

መቀመጫቸውን በኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የነበሩ 2 ሺህ 309 የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደምህት) ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ገቡ።

ወታደሮቹ ዛላንበሳ ሲደርሱ በህብረተሰቡ ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

በዛሬው ዕለት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ወታደሮቹ በትግራይ መንግስት አስፈላጊው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ህብረተሰቡ ይቀላቀላሉ ተብሏል።

ወታደሮቹ ከስልጠናው በኋላ ወደ ህብረተሰቡ በመግባት በሰላምና ልማት ግንባታው የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንዲሁም የትግራይ መንግስትና ህዝብ ወደ ሀገር ውስጥ ለገቡት የደምህት ወታደሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደምህት) መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበልና የትጥቅ ትግል በማቆም ነው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት። (ኤፍ.ቢ.ሲ)