ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ የዛሬውን ጨምሮ ከስድስት ክፍለ ከተሞች ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ሲሉ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባው ትናንት ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውይይቱ ወቅት ወጣቶች የሥራ ማጣት፣ የመሥሪያ ቦታና ሼዶች፣ የወሳኝ ኩነቶችና የመታወቂያ አሠጣጥ ችግሮች እንዲሁም የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ወጣት ፎዚያ ናስር የመሥሪያ ቦታ፣ የሼዶችና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉብን መንግስት ሊፈታልን ይገባል ብላለች።

በቅርብ ላሉ ኃላፊዎች ችግራችንን ብንናግርም በቅርቡ ይፈታል ከማለት ውጭ ያመጡልን መፍትሄ የለም ነው ያለችው።

ወጣት ቢኒያም ከበደ በበኩሉ የመልካም አስተዳደር ችግር አለብን፣ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እየተፈታልን አይደለም ጥያቄዎቻችንን ለሚመለከተው አካል ብናቀርብም ምላሽ እያገኘን አይደለም ብሏል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ብንደራጅም በአግባቡ ሥራ አላገኘንም ያለው ወጣት አስረስ ጌታነህ ደግሞ መንግስት ትኩረት እንዲሠጣቸው ጠይቋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ሼዶች በማን እንደተያዙ በማጣራት ላይ ነን፣ የማጣራቱ ስራ ሲጠናቀቅ ለሚመለከታቸው ሰዎች ይተላለፋሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው የሼዶችን ጉዳይ በማጣራቱ ስራ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

ስለ መኖሪያ ቤት ለተነሳው ጥያቄም በከተማዋ የማጣራት ስራ በመስራት ለደሃ ደሃ የህብረተሰብ ክፍሎች የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሼዶች፣ የቀበሌ ቤቶች፣ ሱቆችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለህብረተሰቡ ሲተላለፉ በግልጽ ነዋሪውን በማሳተፍ ለተገቢው ሰው ይተላለፋሉ ሲሉም አክለዋል።

የመልሶ ማልማት ስራም ዜጎችን ሳያፈናቅል በያሉበት የሚከናወን ይሆናል፣ የግብር አሰባሰብን ፍትሃዊ የማድረግና ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው።

ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ የዛሬውን ጨምሮ ከስድስት ክፍለ ከተሞች ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል።(ኢዜአ)