የአገርና ህዝብ ሰላምን ከማረጋጋት አኳያ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር እየሠራ መሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ

የአገርና ህዝብ ሰላምን ከማረጋጋት አኳያ ከተለያዩ  የአገር ውስጥ  የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ  በመሆን  እየሠራ እንደሚገኝ  የሰማያዊ  ፓርቲ  አስታወቀ ።

የሰማያዊ ፓርቲ በዛሬው ዕለት በሠጠው መግለጫ እንደገለጸው በህዝብ መስዋትነት የተገኘው ድል በአስተማማኝ  መሠረት ላይ ፀንቶ እንዲቆም በመላ አገሪቱ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከምን ጊዜውም በላይ የሰላም እየሠራ  ይገኛል ።

በፌደራሉ ሥርዓቱ አወቃቀርም ሆነ በህገ-መንግሥቱ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችም ካሉ ግጭትና  ንትርክ በመፍጠር ለለውጡ መሰናክል ከመሆን ይልቅ  በህዝብ ፍላጎት ውይይት በማድረግ መፍትሄ መፈለግ  አማራጭ መሆኑን  ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚያምን መግለጫው ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የዜጎች አሰቃቂ ሞት ፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ለአገር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን  መግለጫው አትቷል ።

ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተስተዋሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ያስተላለፉት ውሳኔዎች  ተግባራዊነታቸው እንዲጠናከር ሰማያዊ ፓርቲ ድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል ።

በመጨረሻም ሰሜያዊ ፓርቲ ዜጎች በግጭት ምክንያት  ከመኖሪያ  ቀያቸው እንዳይፈናቀሉ ህዝብ ፣ መንግሥት ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም ጥሪ አቅርቧል ።