ለውጡን ለማስቀጠል የተጀመሩት አገራዊ የሪፎርም ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መንግስት አስታወቀ

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡትን የለውጥ ውጤቶች ለማስቀጠልና ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ የተጀመሩት አገራዊ የሪፎርም ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲል መንግስት አስታወቀ።

ለውጡ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መላው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፏል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው ሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫ አገሪቷ ያጋጠሟትን ችግሮች በዘለቄታው መፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ለምርጫ የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን መንግስት ከልብ ያምናል ብሏል።

በኢትዮጵያ ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ሊረጋገጥ የሚችለው ዜጎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የልማት፣ የፍትህ ፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአግባቡ ሲመለሱ ብቻ መሆኑን በጥብቅ እንደሚገነዘብም አመልክቷል።

“ከዚህ በመነሳትም የሕዝባችንን ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፤  በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግሥት የጀመረውን አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተቋማዊ ቅርጽ ለማስያዝ እየተንቀሳቀሰ ነው” ብሏል።

መንግስት እያከሄዳቸው ካሉት ከአነዚሀ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መካከልም የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት እና አሰራር ማሻሻል መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።

በዚህም ሕዝብን በግልጸኝነት እና በቅንነት ማገልገል ዓላማቸው ያደረጉ የመንግሥት ተቋማትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

መንግስት ተቋማቱ እርስ በርስ ተናበው እና ተቀናጅተው የሚሰሩ፣ የሕዝብ ሀብትን በቁጠባ የሚጠቀሙ እና ውጤታማ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ይሆኑ ዘንድ አስፈላጊውን የህግ፣ የተቋማት እና የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝም አመልክቷል።

“ተስፋ ሰጪው ለውጥ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መላው ህዝባችን እና ዜጎቻችን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ፣ በተለይም ለአገራዊ ለውጡ ቀጣይነት መሰረት ለሆነው ሰላማችን እንደወትሮው ሁሉ ዘብ ሆነው እንዲቆሙ” ሲል  መንግስት ጥሪ አቅርቧል።(ኢዜአ)