ሰራዊቱ ላነሳቸው ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ እንደሚሰጥ የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናገሩ

ሰራዊቱ ላነሳቸው የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ እንደሚሰጥ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ከኢፌዴሪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄ ካቀረቡ የ2ኛ ክፍለ ጦር ሬጅመንት አባላት ጋር ላለፉት ሁለት ቀናት ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም አባላቱ የደመወዝ፣ የጥቅማ ጥቅም፣ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል እንዲሁም የመብት ጥያቄዎች ማቅረባቸውንም ነው የተናገሩት።

መንግስትም የሃገሪቱን ሁኔታና አቅም ባገናዘበ መንገድ ለደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በያዝነው የ2011 ዓ.ም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።

የአስተዳደርና የመብት ጥያቄዎችን በተመለከተም ከወራት በፊት በተጀመረው የመከላከያ ሰራዊት የማሻሻያ ትግበራ ላይ ምላሽ ያገኛልም ነው ያሉት።(ኤፍቢሲ)