የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች በከፈሉት መስዋትነት ያስጠበቅነው የነጻነታችን ምልክት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ ።
ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ በዛሬው ዕለት በህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት በተከበረው የ11ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓላማው በመፈቃቀድ ላይ የመሠረትነው የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ቃልኪዳን ማህተብ ነው ብለዋል ።
ለሰንደቅ ዓላማው ክብር አኩሪ መስዋትነት እየከፈሉ ነጻ አገር ላስረከቡን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችንን አደራ እያስታወስን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልን ማክበር ይኖርብናል ብለዋል ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው።
ፕሬዚደንት ሙላቱ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማው የብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘላቂ ሰላም ፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት እንዲሆናቸው ዳግም ቃልኪዳን የገቡበት አርማ መሆኑም አያይዘው ገልጸዋል ።
ባለፉት ዓመታትም መንግሥት የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ታሪክ ለመቀየር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣትም ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ።
የአገሪቱ ክብርን ለመመለስና ሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥን ለማረጋገጥም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል ።
ባለፉት 27 ዓመታት ኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት ጥረት እንደተደረገ ሁሉ የፖለቲካዊ ምህዳሩን ለማስፋትና የዜጎች ህዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቂ ሥራዎች ባለመካሄዳቸው ህዘቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል ።
መንግሥት በአገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮችን በመለየትም የዜጎች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል ።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓለማ ቀን “ሰንደቅ አላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ለ11ኛ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ህዝባዊ ተቋማት በመከበር ላይ ይገኛል ።
በመጨረሻም የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንዲከበር ለሚያደርጉት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሌሎች አጋር አካላትን ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል ።
በዓሉን የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲሳካ ትልቅ ጉልበት እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን በሥነሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል ።