መንግስት የአዲስ አበባን ወጣት የማሰር ፍላጎት የለውም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

መንግስት የአዲስ አበባን ወጣት ለይቶ የማጥቃትና  የማሰር ፍላጎት የለውም ሲሉ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣት ስራ ሳይኖረውና በችግር ውስጥ ሆኖ እንኳን  አሁን ላለው ለውጥ ትልቅ መስዋዕትነት የከፈለ እንደሆነ ያስታወሱት ዶክተር አብይ ለዚህ ተግባሩ ምስጋና ብቻ ሳይሆን የመሪነት ሚና ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አዲስ አበባን ማዕከል አድርጎ በመበጥበጥ ብቻ ነው መንግስትን ማዳከም የሚቻለው በሚል አስተሳሰብ ሰላሙን የማይፈልጉ አካላት በዚሁ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ መድበው ለማተራመስ ጥረት ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ምን እየተካሄደ እንደሆነ እንኳን በውል ያልተገነዘቡ አንዳንድ ወጣቶች በትንንሽ ገንዘብ ተደልለው   ወደዚህ ተግባር መሠማራታውንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ሃገርን የማተራመስ አጀንዳውን  በጥልቀት ሳይረዱ ወደዚህ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ወጣቶችን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠን ሲሆን ማስረጃ የተገኘባቸውን አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ዜጎች ሁሉ እኩል ናቸው፣ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የሚባል ነገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ወንጀለኞች ከየትኛውም ብሄርና ከማንኛውም የሥልጣን ደረጃ ቢመጡም በህግ ከመጠየቅ አያመልጡም ብለዋል፡፡

ወንጀለኞቹ ትልቅ አቅም የፈጠሩ በመሆናቸው ወንጀል ሲሰሩ ማስረጃው እንዳይገኝ አድርገው ስለሆነ ለህግ የማቅረቡን ስራ ቀላል እንዳይሆን ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡