የታጠቀ ወታደር ወደ ቤተ መንግስት የመጣው ለውጡን ለማደናቀፍ በማሰብ ነው –ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

የታጠቀ ወታደር ወደ ቤተ መንግስት የመጣው አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ ታሳቢ  በማድረግ እንደነበር  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሠጡበት ወቅት እንደገለጹት ቀደም ሲል ወደ ቤተ መንግሥት የመጣው የታጠቀው ኃይል  አገራዊ  ለውጡን  ለማደናቀፍ ዓላማ ያደረገ  ነው ብለዋል ።   

የወታደራዊ ኃይሉን የማስተባበር ሥራ በአንዳንድ ተንኮለኞች ሴራ ተጠንስሶ የተፈፀመ ነው ያሉት ዶክተር አብይ  ወደ ቤተ መንግሥት ከመጡት ተራ  ወታደሮች በሙሉ  ግን ይህን እሳቤ ይዘው መጥተዋል ለማለት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል ፡፡

መንግሥት  ይህን  የተደቀነ ችግር ለመፍታትም  ጥንቃቄ  የተሞላበት  እርምጃ ባይወስድ ኖሮም አገርን ወደቀውስ ሊከት የሚችል ክስተት እንደነበርም ገልጸዋል ፡፡

በወቅቱ የወታደሮቹን አመጣጥ ወታደራዊ ጥበብ በሚጠይቀው መልኩ ከስሜት በራቀ ሁኔታ ጥያቄዎቻቸውን ለማስተናገድ መቻሉ አገርን የማትረፍ ወሳኝ እርምጃ እንደነበረም  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ገልጸዋል፡፡