ወደ አዳማ ከተማ ሊገባ የነበረ 17 ሽጉጥ ከ45 ጥይት ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

ወደ አዳማ ከተማ ሊገባ የነበረ 17 ሽጉጥ ከ45 ጥይት ጋር መያዙን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ በዛሬው ዕለት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በአሰላና በአዲስ አበባ መስመር ወደ አዳማ ከተማ ሊገባ ነበረ 17 ሽጉጥ ከ45 ጥይት ጋር መያዙን ገልጿል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ልዩ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዋና ሳጅን ወርቅነሽ ገልሜቻ እንደገለፁት ትናንት ከጠዋቱ 1፡30 አካባቢ በአሰላ መስመር ወደ አዳማ መግቢያ ልዩ ስሙ ሶደሬ መንገድ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 2 ሹጉጦች ተይዘዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከቀኑ 10 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ ከአዲስ አበባ ቃሊቲ መነሃሪያ የተነሳው ኮድ 3 – 42617 ኦሮ ሃይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አዳማ ከተማ መግቢያ ላይ ልዩ ስሙ መልከአዳማ በተባለው ስፍራ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ደግሞ 15 ሽጉጦችና 45 ጥይቶች መያዛቸው ነው የተገለጸው፡፡

የጦር መሳሪያው ባለቤት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ታወቋል፡፡

ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ጥርጣሬ የሚያጭሩ የተለዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥመው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ዋና ሳጅን ወርቅነሽ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡(ኢዜአ)