የትግራይ ክልል ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም የክልሉን የስራ እቅድ አፀደቀ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ በትላንትና ውሎው በክልሉ የ2011 ዓ.ም የስራ እቅድ ላይ ተወያይቶ አፀደቀ።

በዚህ አመት በክልሉ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን እና ዴሞክራታይዜሽን ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በክልሉ የሚታየውን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የውጭ ሃገራት ተሞክሮን ወስዶ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።

መንገድ ባልገባባቸው 124 የገጠር ቀበሌዎች በዚህ አመት በክረምት እና በጋ የሚያገለግሉ መንገዶች እንዲሰራ እቅድ መያዙንም አስረድተዋል።

የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እንዲሁም የመድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶችን እጥረት ለማቃለል በዚህ አመት በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት።

የትምህርት ጥራትን ማሻሻል ላይ እና በጎልማሶች ትምህርት ልዩ ስራ ይሰራል ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፥ በሁሉም ዘርፎች የሚሰሩ ስራዎች በጥናት፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ የታገዙ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

በእቅድ ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ሲሆን፥ በተለይ እቅዱ ሰፊ ከመሆኑ አንፃር በአፈፃፀሙ ዙሪያ ክፍተት እንዳይታይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተብሏል።

ዶክተር ደብረጽዮን በበኩላቸው በክልሉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና የድህነት መጠኑን ለመቀነስ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በክልሉ በስብሰባ ምክንያት የሚስተጓጎል የመንግስት አገልግሎት የለም ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፥ በዚህ ምክንያት የመንግስት ስራ በሚያስተጓጉሉ ሰራተኞች እና አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል።

ምክር ቤቱም በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የስራ እቅድ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን የክልሉን የከፍተኛ ፍርድ ቤት እቅድም አድምጧል::

ምክር ቤቱ በዛሬው እለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፥ የክልሉን ዋና ኦዲተር እቅድ እና የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል:: (ኤፍ.ቢ.ሲ)