ዘንድሮ ለሚከበርው የብሔር ብሔርሰቦችና ህዝቦች ቀን ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የፌደረሽን ምክር ቤት አስታወቀ

ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ለሚከበርው የብሔር ብሔርሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ቀኑ “በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት ቀን እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የፌደሬሽን  ምክር ቤት አፈጉባኤ  ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም  ትናንት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አዘጋጅነት ለሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን አስፈላጊው ቀድመ ዘግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ።

የበዓሉ አስተባባሪ አብይ ኮሚቴም አስቀድሞ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ተናግረዋል፡፡

የበዓሉን አከባበር ፋይዳ አስመልክቶ ጥናት መደረጉን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ ባህልን፣ ቋንቋና ማንነትን ማዕከል ባደረገ መልክ እንዲከበር መወሰኑ የተመላከተ ሲሆን ከበዓሉ አላማ አኳያ የብሄራዊ ማንነት እና ኢትዮጵያዊ ማንንትን አቀናጅቶ ከመሄድ አኳያ ጉድለቶች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

ህዳር 29 የሚከናወነው በዓል በተለየ መልኩ በህዝቦች መካከል የላቀ መቀራረብ እንዲፈጠር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውኖ እንደሚከበርና ይህም በህዝቦች መካክል ለተፈጠረው ችግር ህዝቡ በራሱ መፍትሔ መሥጠት እንዲችል እድል እንደሚሰጥ አፈጉባኤዋ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ  በዋና ከተማው ለሚታደምበት  በዓል አስፈላጊው ቅደመ ዘግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡

በዓሉ ለሁለተኛ ጊዜ በከተማዋ እንደሚከበር የገለጹት ምክትል ከንቲባ ለወጣቶች የስራ እድል በሚፈጠርበት አግባብ ታልሞ የተዘገጀ እንደሆነ እና በበዓሉ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የሚወጣበት በዓል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው በዓል ኢትዮጵያዊ ማንነት ከብሔራዊ ማንንት ተጣምሮ እጅግ በደመቀ መልኩ አንደሚከበር አብይ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡