የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በዛሬው ዕለት ባደረጉት 2ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለርዕሰ ብሔርነት ኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄን ተቀብለዋል ።
ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዛሬው ዕለት በጋራ ምክር ቤቶቹ ላይ በመገኘት የሥራ ስንብት ወይም ከሃላፊነት የመልቀቅ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል ።
ፕሬዚዳንቱ ለምክር ቤቶቹ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት አምስት ዓመት በፊት ሁለቱም ምክር ቤቶች ባደረጉት ስብሰባ በሙሉ ድምጽ በፕሬዚደንትነት እንድመረጥና በሥራ ዘመኔ ሙሉ ትብብር ላደረጉላቸው የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ የታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ።
በአምስት ዓመት ውስጥ አቅሜና በፈቀደ ሁሉ የተጣለብኝን ኃላፊነት በታማኝነት እንደፈጸምኩ ይሰማኛል ብለዋል ፕሬዚደንቱ ።
ከስድስት ወራት በፊት አገሪቷ በመስቀለኛ መንገድ ነበረች ያሉት ፕሬዚደንት አሁን ግን በአገሪቱና በህዝቦቿ ዘንድ የተስፋ ጎህ ቀዶ ቀዷል በማለት ገልጸዋል ።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ከሰባት ወራት በፊት በአገሪቱ እንደዚህ ዓለምን ያስደመመ ለውጥ ይመጣል ብሎ ያመነም ያሰበም እንደሌለ ጠቅሰዋል ።
በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እስረኞች እንዲፈቱ በውጭ በትጥቅ ትግል የሚገኙ ኃይሎች በሰላም ወደ አገራቸው ገብተው በሰላም የሓሳብ ትግል መፈቀዱ ሌላው የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ያሰደነቁ ተግባራት እንደነበሩ ጠቁመዋል ።
ኢትዮጵያና ኤርትራም ከነበሩበት ወጥተው ሕዝቦቻቸው በፍቅር፣ በአንድነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር መቻላቸው ሌላው የለውጥ መገለጫ መሆኑን ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው አስረድተዋል ።
በአገራዊ ለውጡ ቀላል የሚመስሉ ቢሆንም ለነገ አገራዊ ለውጥ ትልቅ ስንቅ እንደሚሆንም ፕሬዚደንቱ አስገንዝበዋል ።
በአገሪቱ በረጅም ጊዜ የታቀዱ ረዕዮችን ለማሳካትና ዘለቂነት ለማስጠበቅ ህዝቡን በማስተባበረ መሥራት እንደሚያስፈልግም ፕሬዚደንቱ ጠቁመዋል ።
በአገሪቱ የሰፈነውን ድህነትን፣ ኃላቀርነትና መሃይምነትን በማስወገድም የዜጎችን ተጠቃሚነትን ማሳደግም ይገባል ብለዋል ።
በአገሪቱ አሁን የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በዘላቂነት ለማጠናከርን ጠንካራና ተጠያቂ ተቋማትን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል ።
ዜጎች በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አውድ አገሪቱን ወደ ሌላ ሁኔታና አደጋ የሚወስድ በመሆኑም ማንኛውንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ በብሔር መነጽር ብቻ ማየት መቀጠል የለብንም ብለዋል ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው ።
ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በርዕሰ ብሔርነታቸው ወቅት ለውጡን ለማየትና አካል መሆን በመቻላቸው ኩራት እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል ።
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ይዤ የቆየሁትን አገራዊ ኃላፊነት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ውሳኔ ላይ የደረስኩ በመሆኔ የተከበሩት ምክር ቤቶች ኢፌዴሪ ፕሬዚደንትነት ኃላፊነቴ እንዲያሰናብተኝ እጠይቃለሁ ብለዋል ።