አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን  ምክር ቤቶች  በዛሬው ዕለት ባደረጉት  የጋራ ልዩ ስብሰባ  አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት  በማድረግ በሙሉ ድምጽ  መርጠዋል ።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በጋራ  ምክር ቤቶቹ ልዩ  ስብሰባ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ለመሆን  ብቸኛ  እጩ ሆነው የቀረቡ  ሲሆን  በአገር ውስጥና  በዓለም አቀፍ ደረጃ  ያካበቱት  የሥራና የኃላፊነት  ልምድ   የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት  ለመሆን  ተመራጭ እንዲሆኑ ማድረጉን የህዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  አቶ ታገሰ  ጫፎ ተናግረዋል።

አቶ ታገሰ እንደገለጹት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፕሬዚደንት  በእጩነት የተመረጡት ያላቸውን የትምህርት ደረጃ ፣ የዲፕሎማሲ የካበተ ልምድ ፣ በዓለም አቀፍ  ደረጃ ኢትዮጵያን በመወከል ለረጅም ጊዜ ማገልገላቸው  ከግምት  ውስጥ ገብቷል ብለዋል  ።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ  በኢትዮጵያ  የመጀመሪያዋ ሴት አምባሳደር ከሆኑት ዮዲት እምሩ  ቀጥሎ  በኢትዮጵያ  ሁለተኛው ሴት አምባሳደር  መሆናቸውን  አቶ ታገሰ  ለምክር ቤቱ ተናግረዋል ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራር ደንብ መሠረት አምባሳደር ሳህለወርቅን በኢፌዴሪ ፕሬዚደንትነት ለመምረጥ  የምክርቤቶቹን  2/3ኛውን ድምጽ  ማግኘት  ስለነበረባቸው የምክርቤቶቹ አባላት ድምጽ እንዲሠጡ ተደርጓል ።

በምክር ቤቶቹ  የድምጽ አሠጣጥ ውጤትም  አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ  የምክር ቤቶቹን  ሙሉ ድምጽ በማግኘታቸው  4ኛው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት በመሆን ተመርጠዋል ።

 አምባሳደር ሳህለወርቅ የፌደራል ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ኃላፊ በተገኙበት  ቃለ ማሃላ ፈጽመዋል ።      

በመጨረሻም  የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ  ተሾመ አዲስ ለተመረጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ  ሥልጣናቸውን አስረክበዋል ።