የአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ

የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መመረጥን ተከትሎ ባወጡት መግለጫ ነው የእንኳን ደስ ያሎት መልእክት ያስተላለፉት።

ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ተደርገው በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸውን አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሴት ትልቅ ሀላፊነት ስትረከብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር፤ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ያደረገችው ጾታዊ ተዋጽዖን የጠበቀ ካቢኔ ምስረታና የሴት ፕሬዚዳንት ምርጫ ሀገሪቱ ሴቶችን ከማብቃት አኳያ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯን ያሳያል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም የእንኳን ደስ ያልዎት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀጣይ ስራቸውም ስኬትን ተመኝተዋል።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት አክለውም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት እና ለኢትዮጵያ ፓርላማም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ ማስተላለፉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢጋድ ዋና ፀሀፊ አምባሳደር ማህቡብ ማዐሊም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት አንኳን ደስ አላቹ ብሏል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት በመምረጧ በከፍተኛ የመንግስት አመራር ላይ እንዲወጡ ትልቅ ታሪክ ሰርታለች ሲሉ ዋና ፀሀፊው ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን ትልቅ ዕውቀት እና ልምድ ተጠቅመው የኢትዮጵያን እና የአከባቢዋን ጥቅም በሁሉም መስክ ለማራመድ ይጠቀሙበታል ሲል ኢጋድ አስታውቋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)