የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኑዮ ጉቴሬዝ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የደስታ መግለጫ አስተላለፉ።

ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው የእንኳን ደስ አለዎት መልእክቱን ነው ያስተላለፉት።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አክለውም ለመላው ኢትዮጵያን ባስተላለፉት መልእክት፥ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት በመምረጣችሁ እና አዲስ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ሀላፊነት እንዲይዙ በማድረጋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

አፍሪካ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ ሀላፊነት በማምጣት ለሌሎች አርአያ በሚሆን መልኩ ቅድሚያ በመውሰድ እየሰራች ነው ያሉት ዋና ፀሃፊው፤ የሴቶች አመራር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑንም እያረጋገጡ መሆኑንም ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የደስታ መግለጫ ልከዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዚዳንት መምረጧ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካ ብሎም ለመላው ዓለም ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው።

ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ በፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ አይበገሬ አፍሪካ ሴቶች ዕጣ ፈንታ እየተቀየረ ለመሆኑ ማሳያ ነው ፕሬዝዳንት ኬንያ በመግለጫቸው ያስታወቁት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኬንያ ባለው የተመድ ጽህፈት ቤት ውስጥ በዳይሬክተርነት ሲሰሩ በተለያየ ጊዜ ተገናኝተው ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንት ኬንያታ፥ ይህ ግንኙነታቸውም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚረዳ ነው ያስታወቁት።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)