ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በሚመሩት ውይይት ላይ ለመሳተፍ ወደ ፍራንክፈርት እየገቡ ነው

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በጥቅምት 21፤ ቀን 2011 ዓ.ም ለሚደረገው የውይይት መድረክ ለመሳተፍ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት መግባት ጀምረዋል፡፡     

ኢትዮጵያውያኑና በአውሮፓ ከሚገኙ 12 ኤምባሲዎች የተወከሉ ዲፕሎማቶች ፍራንክፈርት እየደረሱ ሲሆን መድረኩ “በአንድነት እንነሳ፣ ነገንም እንገንባ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራው ብሄራዊ ኮሚቴ ከበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የፍራንክፈርት የቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የዳያስፖራ አባላት ጋር በመሆን ለስነስርዓቱን ዝግጅት አጠናቋል፡፡            

ኮሚቴው የእስከአሁኑን ዝግጅትና አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡          

የፍራንክፈርቱ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን 200 የበጎ ፍቃድ ሠራተኛ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉም ታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰሜን አሜሪካ  ከጥቂት ወራት በፊት ያደረጉት ጉብኝት ቀጣይ ምዕራፍ የሆነው ይኸው መድረክ የአንድነትና የፍቅር ድልድይ በመገንባቱ የተፈጠረው የህብረት መንፈስ ለአገር ግንባታ ማዋል እንዲቻል ጥሪ ይቀርብበታል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡