ሀገራዊ ለውጡ ከግብ እንዲደርስ ሴቶች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥ አንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ ሴቶች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስና የጀግኒት ቅናቄ ፕሮግራም በይፋ የማስጀመር ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልና የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለምፀጋይ አሰፋን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች ተሳትፈዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን ገልጸው፤ ይህ ሀገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ እና ከግብ እንዲደርስ ሴቶች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዳበረ የግጭት አፈታትና የእርቅ ባህል ያላት ሀገር ነች ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ የኢትዮጵያ ሴቶችም ይህንን ማስጠበቅ እና ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አልከውም፥ ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁላችንም ለሰላማችን ዘብ መቆም አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ሰላም በሀይል ሳይሆን ከግለሰብ ውስጣዊ ሰላም የሚመነጭ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሰላም ዙሪያ ጽንሰ ሀሳብ እና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ወደ ሀላፊነት የመጡ ሴቶችም ሰላም ማስጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ከዚህ ባለፈ ግን ድምጻቸው ላልተሰማ እና ለተቸገሩ ሴቶች መድረስ እንዳለባቸውም አስረድተዋል።

የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አሁን ላይ ሴቶች በብዛት ወደ ከፍተኛ ሀላፊነት የመጡት በርካታ ሴቶች በከፈሉት መስዋእትነት ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት አያይዘውም፥ ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ ነው፤ ስለ ሰላም ደግሞ መጀመሪያ ሀላፊነት መውሰድ ያለባቸው ሴቶች ናቸው ብላዋል።

በተለይም እናቶች ለልጆቻቸው ስለ ሰላም አስፈላጊነት ከመንገር ጀምሮ በበርካታ መንገዶች ትውልዱን የመቅረጽ ሀላፊነት አንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ሴቶች ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ሴቶች የሚጠበቅባቸውን የሚና እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑንም ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት ያስታወቁት።

መንግስት ለሴቶች የሰጠው ሀላሂነት “አይቻልም እና አይችሉም” የሚለውን አስተሳሰብ ያስቀረ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ሴቶችም ያላቸውን እምቅ አቅም በማውጠጣት የተሰጣቸውን እድል ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለምፀጋይ አሰፋ፥ የኢትዮጵያ ሴቶች ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ጠንካራ ሀገራዊ የሰላምና የልማት መነሳሳት በተፈጠረበት ጊዜ መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)