አደረጃጀቱ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ሥር የሆነና የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሥራን ተክቶ የሚሠራ የፕሬስ ሴክረቴሪያት ተቋቋመ ።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያትን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ እንደተገለጸው አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ተሾመዋል ።
በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ሥር በተቋቋመው የፕሬስ ሴክሬተሪያትም ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም በኃላፊነት ተሾመዋል ።
የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን የመጀመሪያው ቀን መግለጫቸውን ሠጥተዋል ።
ወይዘሮ ብልለኔ በመግለጫው እንደጠቆሙት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት መታጠፉንና አዲስ የተቋቋመው ሴክሬተሪያት መረጃን በግልጽ ለመሥጠትና ከሚዲያው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚሠራ ነው ብለዋል ።
የፕሬስ ሴክሬተሪያቱ በተለያዩ ባለሙያዎች የተደራጀና የዳበረ እንደሚሆነው ይሠራል ብለዋል ።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባፀደቀው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ታጥፏል በምትኩም በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ሥር የተቋቋመው የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊነቱን ወስዶ ሥራውን መጀመሩን ወይዘሮ ቢልለኔ ገልጸዋል ።
ሴክሬተሪያቱ ከተለያዩ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና ከተለያዩ የክልል መንግሥታት ጋር በመሆን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ የመሥጠት ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል ።
የፕሬስ ሴክሬተሪያቱን አሠራርና አወቃቀር በተመለከተ በቀጣይ በሚሠጥ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን የሚገለጽ መሆኑንም ወይዘሮ ቢልለኔ ጠቁመዋል ።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ለመገናኛ ብዙሃን በተሻለ መልኩ መረጃን ለማቅረብ ቃል በገቡት መሠረት በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣነ የተመዘገቡ ጋዜጠኞች ቋሚ የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት መግቢያ ተዘግጅቶላቸው መግለጫዎችን የሚያተፉበት ምቹ ሁኔታ ም መፈጠሩን ወይዘሮ ቢልለኔ አስረድተዋል ።