አቶ እንደሻው ጣሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው ተሾሙ

አቶ እንደሻው ጣሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል በመሆን ተሾሙ።

የቀድሞው ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ዘይኑ ጀማል የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው አቶ እንደሻው ጣሰው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው መሾማቸውን የፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ክፍል መረጃ ያመለክታል።

አቶ እንደሻው ከ1983 እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ከመምህርነት እስከ ክፍለ ጦር አመራርነት በትምህርቱ ዘርፍ አገልግለዋል።

ከዚያም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች በትጋት የህዝብንና የመንግስትን ሃላፊነት ሲወጡ የቆዩ ናቸው።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ በምክትል አስተዳዳሪ ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባው የህዝብ ግንኙነት አማካሪ እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።

በትምህርታቸውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጅማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በውጭ ሃገር ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት አጠናቀዋል።