ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአማራ ክልል ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከያዝነው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዓርብ ጎንደር ከተማ የሚገቡ ሲሆን፥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አቀባበል ያደርጉላቸዋል።

በቆይታቸውም በጎንደር እና አካባቢው የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን እና የልማት ስራዎችን እንደሚጎበኙ፥ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ሞገስ ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ በርካታ ኤርትራውያን በተለያየ ስራ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሃገር ደረጃ የተጀመረውን ግንኙነት ያጠናክራል ተብሎም ታምኖበታል።

ፕሬዚዳንቱ የጎንደር ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ባህርዳር እንደሚያቀኑም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የተመራ የልዑካን ቡድን በአስመራ ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ነው።