የሶስቱ አገራት መሪዎች በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ትስስር ስምምነት ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚያዊ ውህደት ስምምነት ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ትናንት ማምሻ ወደ ባህርዳር አምርተዋል።

የአገራቱ መሪዎች በአማራ ክልል ለሚያደርጉት ጉብኝት ትላንት ማለለዳ ጎንደር ከተማ የገቡ ሲሆን የጎንደርን ጉብኝት አጠናቀው ወደ ባህርዳር ከተማ አቅንተዋል።

የሶስቱ አገራት መሪዎች ወደ ባህርዳር ያቀኑት መሪዎቹ፤ ባለፈው ነሐሴ 2010 ዓ.ም በኤርትራ ርዕሰ መዲና አስመራ በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በተፈረመው ስምምነት ላይ ውይይት ለማካሄድ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኤርትራ ሁሉን አቀፍ የሶስትዮሽ ስምምነት ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም አስመራ ላይ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ የሶስቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል።

መሪዎቹ ባህር ዳር በሚኖራቸው ቆይታም የሶስትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኤርትራና የሶማሊያ ፕሬዚዳንቶች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አማካኝነትም ስለ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ገጽታ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

በጎንደር በነበራቸው ቆይታም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገዱ አንዳርጋቸው ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአጼ ቴዎድሮስ ምስል ያለበትን ፎቶ ግራፍ እና ለሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ የፋሲል ግንብ ቅርጽን በስጦታ መልክ አበርክተዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውም ለሁለቱ አገራት መሪዎች የጎንደር የባህል አልባሳትን ያበረከቱ ሲሆን የጎንደር ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አድሃነ በበኩላቸው ለሶስቱ አገራት መሪዎች የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ አርማ ያለበትን ስካርቭ አበርክተዋል።

የኤርትራና የሶማሊያ ፕሬዚዳንቶች ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በደማቅ ሁኔታ ሽኝት አድርገውላቸዋል። (ኢዜአ)