በመተማ ዮሐንስ በተከፈተ ተኩስ በሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተገለጸ

በመተማ ዮሐንስ ቤት ውስጥ ተደብቀው ተኩስ በከፈቱ አካላት በሰዎች ላይ የሞትና የአካል መቁሰል አደጋ መድረሱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ጌትነት አልታሰብ  እንደገለፁት  ግለሰቦቹ በከፈቱት ተኩስ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ20 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

ከተጎጂዎች መካከልም አንድ የፀጥታ አካልን ጨምሮ ሴቶችና ወጣቶች ይገኙበታል ብለዋል።

የቅማንት ማህበረሰብ ተቆርቋሪ ነን በሚሉ አካላት ጉዳቱ ሊደርስ መቻሉንም ኃላፊው ገልፀዋል።

ጉዳቱን ካደረሱት አካላት መካከልም አራቱ እጃቸውን የሠጡ ሲሆን ቀሪዎቹም በሰላማዊ መንገድ ለፀጥታ ኃይሎች እጃቸውን እንዲሠጡ እየተጠየቁ ስለመሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ጉዳት ካደረሱት ግለሰቦችም 9 የክላሽንኮቭ፣ አንድ ኤፍ ኤን መሳሪያ፣አንድ ሽጉጥ፣ አንድ ቦንብና በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር ስራ መዋላቸውን  ኮማንደር ጌትነት አስታውቀዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመተማ ዮሐንስ ጤና ጣቢያ፣ በገንዳ ውሃ ሆስፒታልና በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረጋላቸ ነው ብለዋል።

ለዘመናት ተሳስሮ በኖረው የአማራና የቅማንት ማህበረሰብ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ኮማንደሩ፤ ችግሩ እስኪበርድ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ህብረተሰቡን በማስተማር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና  ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ ጥፋተኞችን በመለየት ለህግ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።

የተፈጠረውን  ግጭት ላማረጋጋት የመከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፖሊስ አባላትና የአካባቢ ሚሊሻዎች በጋራ በመሆን ወደ  እየሰሩ ናቸው ሲሉ ኮማንደሩ ጠቅሰዋል፡፡(ኢዜአ)