ከ40 በላይ የሚሆኑ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮችና የደህንነት አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ከ40 በላይ የሚሆኑ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ አመራሮችና የደኅንነት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቆመ፡፡

የሜቴክ ከፍተኛ አመራሮችና የደኅንነት አባላት ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ለስብሰባ ከተጠሩበት ስፍራ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሪፖርተር ጋዜጣ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እንደ ምንጮቹ ገለጻ ከፍተኛ አመራሩና የደኅንነት አባላቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ገርጂ አካባቢ በሚገኘውና ቀድሞ ኢምፔሪያል ሆቴል ተብሎ ይጠራ በነበረውና አሁን የኮርፖሬሽኑ ንብረት በሆነው አሞራው ሕንፃ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አመራሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉበት ምክንያት ባይገለጽም የፌዴራል ፖሊስ ጊዜያዊ እስር ቤት በሆነው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማቆያ ቤት መታሰራቸውን ምንጮቹ አክለዋል፡፡