በተደራጀ ሌብነትንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የሚወሰዱት እርምጃዎች የህግ በላይነትን የሚያረጋግጡ ናቸው -የህግ ባለሙያ

መንግስት የተደራጀ ሌብነትንና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል የሚወስዳቸው እርምጃዎች የህግ በላይነትን የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተሾመ ወልደኃዋሪያት ተናገሩ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሙያ አቶ ተሾመ ወልደኃዋሪያት ባለፉት ስድስት ወራት መንግስት በህግ መግዛት እንዲኖር እና ለህግ በላይነትን  ለማረጋገጥ  የለውጥ  ሂደት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግስት በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና አተገባበር እንዲሁም በኢኮኖሚ ዘርፍ በተደራጀ መልኩ የተፈጸመው  ዝርፊያ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡         

አሁን በህግ ጥላ ሥር እየዋሉ ያሉ ተጠርጣሪዎች  ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ያሉት አቶ ተሾመ ወደ ፊት በነጻ ፍርድ ቤቶች ቀርበው ሲዳኙ ፍትሕ ይረጋገጣል ብለዋል፡፡  

ከዚህ በፊት የታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይደገም ከታየው የህግ ጥሰት እንደ አገር መማር እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡        

ሰሞኑን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ በጠቅላይ አቃቤ ህግ የተሠጠው መግለጫ በሰው ልጆች ላይ ሊፈፀም የማይገቡ ዘግናኝ ድርጊቶች ናቸው ያሉት የህግ ባለሙያው በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተመጣጣኝና አስተማሪ የሆነ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ አክለዋል፡፡

ህብረተሰቡም አስፈላጊውን መረጃ በመስጠትና በመተባበር የተደበቀ ነገር ካለ በማጋለጥ ወደ ፍርድ እንዲቀርብ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡