የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መስዋዕትነት የከፈለው የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ነው…የክልሉ መንግስት

የትግራይ ህዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት በሃገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ለዋልታ  በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግስት  የህግ የበላይነትን የማስከበር  የጀመረውን ሂደት በተገቢው ጥንቃቄ ሊከናወን የሚገባውም  ገልጿል ።

በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና በፈጸሙ ሰዎች ላይ መንግስት ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የህግ ልዕልና ሳይሸራረፍ ከተጽዕኖ በፀዳ መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም በመግለጫው ተመልክቷል።

የትግራይ ህዝብ ለዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት የህግ የበላይነት እንዲከበርና በማንኛውም ወቅት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው መንግስት እየወሰደ  ባለው እርምጃ  በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲያተኩር ጠቁሟል።

የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሙስና ችግርና በህገ-መንግስታዊ ጥሰት  በአመራሮችና ተቋማት ችግር መሆኑን ቀደም ሲል በተካሄዱ የኢህአዴግ የስብሰባ መድረኮች ላይ በግልጽ ውይይት መደረጉንም አመልክቷል።

ችግሩ በእኩል እንዲስተናገድ ከማድረግ ባለፈ እርቅና ይቅር ባይነትን መሠረት በማድረግ የተጀመረው ሂደት እንዲከናወንና የተጀመረው ለውጥ  ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል መግለጫው።

“የህግ የበላይነትም ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚጠይቅ መሆኑንም የክልሉ መንግስት ያምናል” ሲልም አስታውቋል፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የከፈለው መስዋዕትነት የዜጎች ፍትህ ፣እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት እንዲከበር እንጂ በማንም አካል እንዲጣስ እንዳልሆነ መግለጫው አመልክቷል።

ባለፉት ዓመታት ይታዩ የነበሩት የፍትህና የዲሞክራሲ መጓደሎች እንዲስተካከሉ ህዝቡ በፅናት እየታገለ መምጣቱንም መግለጫው አስታውሶ በጥልቅ ተሓድሶ ወቅት ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድቷል።

ከሰብአዊ መብት አያያዝና ከሙስና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እየታየ ላለው ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እጃቸው ያለበት አመራሮችና ተቋማት መሆናቸውንም መግለጫው አመልክቷል።