የሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሄራዊ እርቀ ሰላም እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽን እንዲቋቋሙ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤት ባሳለፍነው ረቡዕ ባካሄደው ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በዚህም ምክር ቤቱ በቀረበው የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ነው የተገለፀው።

የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነት እና ፍትህ ላይ መሠረት ያደረገ እርቅን ለማውረድ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ቀጥሎም የማንነትና አስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን ለሟቋቋም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።

ኮሚሽኑ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን እና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ችግሮችን ሀገር አቀፍ በሆነ እና በማያዳግም መልኩ ለመፍታት እንዲሁም ከወሰን አስተዳደር ጋር ተያይዞ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለው እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በስብሰባው ለልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል የኢፌዴሪ መንግስትና እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገው የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ እንዲፀቅም ለህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ልኳል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻም መንግስት በቅርቡ ያደረገውን ለውጥ ተከትሎ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 መሠረት የተደራጁትን የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን፣ የውሃ ልማት ኮሚሽን፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ባለስልጣን እንዲሁም የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲቲዩትን ሥልጣን፣ ተግባር እና አደረጃጀት ለመወሰን ተዘጋጀው በቀረቡ ረቂቅ ደንብ ላይ በስፋት ተወያይቷል።

ምክር ቤቱ ከውይይቱ በኋላም ደንቦቹ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡ እና ስራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል።(ኤፍቢሲ)