የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደሚያወግዘው አስታወቀ

ከድርጅቱ ተልዕኮና ባህሪ እጅግ ባፈነገጠና በተቃረነ አግባብ የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም ስልጣንን ለሽብር ተግባር የማዋል ድርጊቶችን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደሚያወግዘው አስታወቀ፡፡

በህገወጥ ድርጊቶች የተሳተፉ አካላት ተገቢ የሆነ ህጋዊ እርምጃ እንድወሰድባቸው ንቅናቄ ኮሚቴው የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በህገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ወይም ሀይሎች የትኛውንም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ የማይወክሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ህብረተሰባዊ ለውጥን ለማፋጠን የተዘረጋውን መንግስታዊ ስልጣን ለግል ጥቅማቸው ማስከበሪያነት የተጠቀሙ በመሆኑ ድርጊቱን በጽኑ እንደሚቃወምም አንስተዋል፡፡

መንግስታዊና ህዝባዊ ሀላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተውና ሥልጣንን መከታ በማድረግ በከፍተኛ ምዝበራ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሽብር ተግባር ስለመሳተፋቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ህጋዊ መንገዱን በመከተል በቁጥጥር ስር ማዋሉና ተገቢውን ቅጣት የማሰረፉ ሂደትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አሳስበዋል፡፡

 

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢ.ፊ.ዲ.ሪ መንግስት ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ከሙስናና ስልጣንን ተገን በማድረግ በተፈፀሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን እርምጃ አስመለክቶ ከደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

ከድርጅታችን ደኢህዴን/ኢህአዴግ ተልዕኮና ባህሪ እጅግ ባፈነገጠና በተቃረነ አግባብ የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችን እንዲሁም ስልጣንን ለሽብር ተግባር የማዋል ድርጊቶችን ደኢህዴን በእጅጉ ይኮንናል፤ ያወግዛል፡፡ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትም ተገቢው ህጋዊ እርምጃ ይወስደባቸው ዘንድ የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡

በዚህ መሰሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ወይም ሀይሎች የትኛውንም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ የማይወክሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ህብረተሰባዊ ለውጥን ለማፋጠን የተዘረጋውን መንግስታዊ ስልጣን ለግል ጥቅማቸው ማስከበሪያነት የተጠቀሙ በመሆኑ ድርጊቱን በጽኑ ይቃወማል፡፡

እንደሚታወቀው በሀገር እና በክልላችን ደረጃ በታላቅ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ለዚህ የለውጥ ሂደት ዳር መድረስ የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎች እና ህብረተሰቡ በአስተሳሰብና በድርጊት በተቀራረበ ሁኔታ በመቀናጀት የለውጡን ፍሬ ለማየት ደፋ ቀና ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ የለውጥ ሂደት መጠናከር ዓይነተኛ ሚና ከሚጫወቱትና ሰፊ የለውጥ ሀይል በማሰባሰብ ለውጡን ወደማይቀለበስ ደረጃ ለማሸጋገር ከሚያግዙት መንገዶች አንዱ ደግሞ የህግ የበላይነትን በተግባር በማረጋገጥ የድርጅትንና የመንግስትን ስልጣን ካባና ተገን አድርገው ህገ-ወጥ ጥፋት በሚፈፀሙ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ የመውሰድ ጉዳይ ነው፡፡

ከድርጅታችን ህዝባዊ ባህሪ በማይመነጭና ከማህበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ ዓላማዎቻችንና ፕሮግራሞቻችን ፍፁም በተፃራሪ ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችንና ግብረ-አብሮቻቸውን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ንቅናቄው ድርሻውን በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ለመወጣት መዘጋጀቱን በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል ፡፡

መንግስታዊና ህዝባዊ ሀላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተውና ሥልጣንን መከታ በማድረግ በከፍተኛ ምዝበራ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሽብር ተግባር ስለመሳተፋቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ህጋዊ መንገዱን በመከተል በቁጥጥር ስር ማዋሉና ተገቢውን ቅጣት የማሰረፉ ሂደትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳስባል፡፡

የለውጡን መሰረት ማስፋትና ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ሂደት አልጋ በአልጋ በሆነ ሁኔታ ሊራመድ እንደማይችል በውል የሚገነዘበው ደኢህዴን፣ ህገ-ወጦችን የመለየቱና እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ህብረተሰባዊ ለውጡን ለማረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንፃር በቁርጠኝነትና በግልጸኝነት መንፈስ ሊፈጸም እንደሚገባው ያምናል፡፡

ደኢህዴን/ኢህአዴግ ከተሸረሸረው ህዝባዊ እምነት በአጭር ጊዜ ተሻግሮ ህዝባዊ እምነቱና ተቀባይነቱ ወደተሻለ ደረጃ ሊሸጋገር የሚችለው በቅድሚያ በዙሪያው የሚገኙ ህገ-ወጦችን ማጥራትና ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ ሲችል በመሆኑ ህገ-ወጥነትን በመግታት ለህግ የበላይነት መስፈን የተጀመረው ጥረት እንዲጠናከር የበኩሉን ይወጣል ፡፡

ደኢህዴን/ኢህአዴግ ራሱን ለማረምና ለመለወጥ ያገኘውን ወርቃማ እድል በጥንቃቄና ሁሉ አቀፍ በሆነ አግባብ መጠቀም እንዳለበት የሚታመን በመሆኑ መላው የድርጅታችን አመራሮችና አባላት እንዲሁም የክልላችን ህዝቦች ህገ-ወጦችን በማጋለጡና የህግ-የበላይነትን በማረጋገጡ ሂደት ውስጥ ከመንግስት ጎን ቆመው ታላቅ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ደኢህዴን ጥሪ ያቀርባል፡፡

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት 

ሀዋሳ