አስተዳደሩ በሜድሮክ ኢትዮጵያ ለረዠም ጊዜ ታጥሮ የቆዬውን መሬት ወደ መንግስት ካዝና በመመለስ የአጥር ማፍረስ ሥራ አከናወነ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሣ አካባቢ በ33 ሺህ 514 ካሬ ሜትር ላይ በሜድሮክ ኢትዮጵያ ታጥሮ የቆዬውን ቦታ ወደ መንግስት ካዝና በመመለሱ በዛሬው ዕለት አጥር የማፍረስ ስራ ተከናውኗል፡፡

ቦታው በ1990 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ በሊዝ ለሜድሮክ ኢትዮጵያ ተላልፎ ከመሥጠቱ በፊት የስፖርት ማዘወተሪያና የጥምቀት ከተራ በዓል የሚከበርበት ስፍራ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ይሁንና መንግስት ቦታውን ለተሓለ ልማት ሲል ለሜድሮክ ኢትዮጵያ በሊዝ አሳልፎ ቢሰጥም ቦታው እስካሁን ድረስ ያለምንም ልማት ሳይውል  ቆይቷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን በወቅቱ ሲሰጥ በአንድ ካሬ በአማካይ ለአንድ ዜጋ የስራ ዕድል ይፈጥራል በሚል ከ33 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በማሰብ የሠጠ ቢሆንም ድርጅቱ የስፍራውን ገጽታ ከማበላሸት ውጭ ለምንም ጥቅም ባለማዋሉ አስተዳደሩ ቦታውን በመቀማት አጥሩንም ወደማፍረስ ስፍራ ገብተዋል ነው የተባለው፡፡

ሜድሮክ ኢትዮጵያ በበኩሉ ቦታውን በሊዝ ከተረከብኩት ወዲህ በተለያዩ ጊዚያት የዲዛይን መቀያየር ስለገጠመኝ ግንባታውን በተቀመጠለት ገደብ ለማጠናቀቅ አዳጋች ሆኖብኛል ነው ያለው፡፡

ድርጅቱ በስፍራው ያሉኝን ንብረቶች ለማንሳትም የተሠጠኝ የአንድ ሳምንት የጊዜ ገደብ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ የተሠጠው የ20 አመታት ጊዜ ከበቂ በላይ በመሆኑ ከዚህ በላይ ዕድል መስጠት እንደማያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ንብረቶቹንም በመስከረም መጨረሻ ላይ እንዲያነሳ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር በከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክ እና ማስተላለፍ ስራአስኪያጅ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡

አሁን ከሜድሮክ እንዲቀማ የተደረገው ይህ ስፍራ መንግስት ለመኪና ማቆሚያ አገልግሎት እና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እንደሚጠቀምበትም አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሰል ሁኔታ ታጥረው የተቀመጡ ከ412 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት እና ከ150 በላይ ስፍራዎች ላይ የሚገኙ የጊዜ ገደባቸው አልፎ በህገወጥ መንገድ ታጥሮ የሚገኙ ቦታዎችን ወደ ከተማ አስተዳደሩ  የመሬት ባንክ በመመለስ ለህዝብ አገልግሎት የማዋል ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡