መርማሪ ፖሊስ በዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም ላይ የሚያደረገውን ምርመራ እንዲያጠናቅቅ ፍርድ ቤቱ የ10 ቀን ጊዜ ፈቀደ

የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ እንዲሁም በግንባታ ላይ የሚገኘው የፎር ፖይንት ሸራተን ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ ዓለም ፍፁም ላይ ፖሊስ የሚያደርገውን ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ የ10 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቀደ ።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት አቶ አለም ፍጹም ሪቬራ ሆቴልና የፕላስቲክ ፋብሪካን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ባላቸው ዝምድና በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ወንጀል ተጠርጥረው ቀርበዋል ። 

በችሎቱ የሜቴክ ቦርድ ሆቴሉ እንዳይገዛ ወስኖ እያለ ሆቴሉን በ128 ሚሊዮን ብር ስምምነት ፈጽመው ውሉ ላይ ግን በ195 ሚሊዮን ብር በመሸጥና የ67 ሚሊዮን ብር ልዩነቱን ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የወሰዱትን ብድር ከፍለውበታል በማለት መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ  አቅርቧል ።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ የሆቴሉ ሽያጭ ሲፈጸም የሽያጭ ግብር ለጉሙሩክ በሻጭ አማካኝነት መከፈል ሲገባው ገዢው ሜቴክ 15 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ተብሎም ውሉ ላይ መፈረሙ ነው በችሎቱ ተገልጿል።

አቶ ዓለም ሪቬራ ሆቴልን ሲሸጡ ያልተገባና ዝምድና ግንኙነትን መሠረት በማድረግ በተጋነነ ዋጋ ግዥ በመፈፀም የህዝብን ገንዘብና ሃብት ባልተገባ ሁኔታ  ተጠቅመዋል በሚል በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ፖሊስ በችሎቱ ገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ በተጨማሪም ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑና የሰው ምስክር ለማቅረብ፣ የቦታዎቹን ዋጋ የባለሙያ ግምት ለማካሄድና ኦዲት ለማስደረግ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሠጠኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የአቶ ዓለም ጠበቆች በበኩላቸው  አብዛኛው ስራ የሰነድ በመሆኑና በዝርዝር ስለቀረበ ተጨማሪ ጊዜ አያስፈልግም፤ አቶ ዓለም በሥራቸው 520 ሰራተኞች ስለሚያስተዳድሩ አገርም የሚጎዳ  በመሆኑ በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በማለት በችሎቱ ተከራክረዋል ።

የአቶ ዓለም ጠበቆች በተጨማሪም አቶ ዓለም ከሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር ምንም አይነት ዝምድናም ትውውቅም የላቸውም ስለዚህ ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀው  ተጨማሪ ጊዜ መፈቀድ የለበትም ብለዋል ።

መርማሪ ፖሊስ  በበኩሉ ተጠርጣሪው  በዋስ ቢወጡ ማስረጃ የማጥፋት፤ ምስክሮች ላይ  ጫና  ያደርጋሉ፤ ዝምድናን በተመለከተም በማስረጃ ማረጋገጥ እችላለው  ብሏል በችሎቱ።

ፍርድ ቤቱ  በሁለቱም ወገኖች  የነበረውን ክርክር በማዳመጥ  የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደ ሲሆን አቶ ዓለም ፍጹም የቀጣይ  ቀጠሮ ህዳር 22 ቅዳሜ ላይ የሚውል በመሆኑ ለህዳር 24 ቀን 2011 ዓም ሰኞ ዕለት እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል ።