ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ጋር ሊያወያዩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ ሊወያዩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አሁን ላይ በሀገሪቱ ስለተጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ እና በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው አስፈላጊ ለውጦች ዙሪያ እንደሚወያዩ ነው የተገለጸው።

ውይይቱ በሚቀጥለው ማክሰኞ ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ እንደሚካሄድም ታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመላክተው በውይይቱ ላይ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ ሀገር የተመለሱ ፓርቲወች በውይይቱ ይሳተፋሉ ተብሏል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰኞ ህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረ ገጽ መመዝገብ ይችላሉም ነው የተባለው።(ኤፍ.ቢ.ሲ)