የብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸዉ የበርካታ አለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡

አልጀዚራ የለውጥ አራማጅ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ ሾሙ ሲል በአርዕስተ ዜናው ዘግቧል፡፡

አልጀዚራ በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ብርቱካን ሚደቅሳን በ2012 የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ትልቅ የቤት ስራ የሆበት ተቋም ሃላፊ ሆነው መሾማቸውን አያይዞ ጠቁሟል፡፡

የብርቱካን ሹመት ቀጣዩን ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ታስቦ እንደተከናወነም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ብርቱካን ሚደቅሳን የሾምናቸው ያላቸውን ህገ መንግታዊ እና የህግ እውቀት መነሻ  በማድረግ መሆኑን እንደገለፁም አስታዉሷል፡፡

የብርቱካን ሚደቅሳ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ወደ ስልጣን መምጣት የአፍሪካ ሃገራት ተቃዋሚዎች የመንግስት ስልጣን ባለቤት ማድረግ ስለመጀመራቸው ማሳያም ነው ብሏል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን የጠንካራ ስብዕና ባለቤት እንደሆኑ የጠቆመው አልጀዚራ ከዚህ ቀደም በዳኝነት ስራቸውና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነታቸው ያላቸውን ታሪክ አንስቷል፡፡

አልጀዚራ በዘገባው ማሳረጊያ በዶክተር አቢይ እየተወሰዱ ያሉትን ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎችም ለውጦች አስታወሷል፡፡

ዘ ሮይተርስ በበኩሉ የኢህአዴግን አገዛዝ በመቃወም ትልቅ ስም የነበራቸው ሰው በለውጥ አራማጁ መሪ ለሹመት ታጩ ሲል ጎላ አድርጎ ዘግቧል፡፡

ዶክተር አቢይ ተቃዋሚዎችን ወደ ታገሉለት የፖለቲካ መድረክ ብቅ ብለው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እየሰሩ ስለመሆኑ የብርቱካን ሹመት ማሳያ እንደሆነም ዘ ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡

ዘ ሮይተርስ አክሎም ከ13 ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ወቅት ሀገሪቱ በገጠማት ችግር ለእስር ተዳርገው የነበሩት ብርቱካን ዛሬ የምርጫ ቦርድን ለመምራት ብቁ ሰው ተብለዋል መባሉንም በዘገባው አስፍሯል፡፡

ሌላኛው አለም አቀፍ የሚዲያ አውታር ሮይተርስ በበኩሉ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑትን ሃሌሉያ ሉሌን ሃሳብ በዘገባው ያካተተ ሲሆን ተንታኙም ብርቱካን ምርጫን ፍትሃዊ ከማድረግ ባሻገር ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊነት ለሚደረግ ሽግግር ወሳኝ ሰው መሆናቸውን አትተዋል፡፡

ቢቢሲም የቀድሞ ዳኛና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሾሙ ሲል ዘግቧል፡፡

ብርቱካን ሰባት አመታትን በስደት ማሳለፋቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ የሳቸው ሹመት የሀገሪቱን ቁልፍ ተቋማት በሴቶች እንዲመሩ ለማስቻል እየተደረገ ያለው ጥረት አካልም እንደሆነ አስታውሷል፡፤

የአብዛኛወ ኢትዮጵያንን እምነት ያጣው የምርጫ ቦርድ ይህን ክብር መልሶ ለመቀዳጀት ብርቱካን የተሻለ ስራ እንደሚሰሩና አቅሙ እንዳላቸው በበርካታ ኢትዮጵያዊያን እምነት እንደተጣለባቸውም አትቷል፡፡

በብርቱካን ሹመት ዙሪያ ቢቢሲ ያናገራቸው ተንታኞችም ስለታማኝነታው በሃገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረላቸው ሰው ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡