የህግ በላይነትን ለማረጋገጥና አስተማማኝ የፍትህ ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለጸ ገለጸ

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ የመስሪያ ቤቱን የአንድ መቶ ቀናት እቅድን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡ ሲሆን የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅና በፍትህ ስርዓቱ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ተቋሙ ከመቼውም በላቀ ሁኔታ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የህግ እና የፍትህ ማሻሻያ ሰራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቶችን ትኩረት ሰጥቶ በመከላከል ተቋሙ የተሰጠውን አገራዊ ኃላፊነት ለማሳካት የባለ አንድ ገጽ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

የሕግ የበላይነት አለመረጋገጥና ደካማ የፍትህ ሥርዓት፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት፣ ደካማ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ እና ሕገ ወጥነትና ስርዓት አልበኝነት በመከላከል እና በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትና የፍትህ ሥርዓትን ግንባታን ማጠናከርና አስፈላጊነትን በእቅዱ መነሻ ሃሳቦች ዙሪያ አብራርተዋል፡፡

የፍትህ አግልግሎት በማሻሻል እና የሰው ሃብት አቅም በመገንባት ሶስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት በህዘዝብና በመንግሰት አመኔታን ያተረፈ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት በመሰራት ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የባለአንድ ገጽ እቅድ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስ የሰብአዊ መብት ጥሰት በፈፀሙ ሰዎች የሕግ ተጠያቂነት የማረጋገጥ፣ የታራሚዎችን መብት አያያዝ ማሻሻል፣ የይቅርታና ምህረት አሰጣጥ ሥርዓቱን በተሟላ መልኩ ለመተግበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በማህበራዊ ድረ-ገጽ የሚታዩ የጥላቻ ንግግር ወንጀል ላይ ሕግ ማውጣትና መተግበር እንዲሁም ሕገ ወጥነት፣ ስርዓት አልበኝነትና የመንጋ ፍትህን ለመቆጣጠር ከአሁን በፊት ታይተው የማይታወቁ ህጎችን የማርቀቅና የማሻሻል ስራዎችን አቅዶ ውጤታማ ለመሆን የሕግና የፍትህ አማካሪ ምክር ቤት በማጠናከርና የሰው ሀይል በማደራጀት በመስራት ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ወቅታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መልስ የሰጡ ሲሆን የወንጀል ፍትህ አስተዳደርን በማጠናከር የህዝብና የመንግስት ንብረት የሚዘውሩ ግለሰቦችን እና በመንግሰት ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጠልና ለዚህም ስኬት የመላው ህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡