ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እየተወያዩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በቀጣዩ ምርጫና በወቅታዊ የአገሪቷ ጉዳይ ዙሪያ እየተወያዩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  አሁን ላይ በሀገሪቱ ስለተጀመረው ዘርፈ ብዙ ለውጥና በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው አስፈላጊ እርምጃዎች ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እየተወያዩ ይገኛል።

ውይይቱ የሚካሄደው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ሲሆን 81  የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራር፣ የገዢው ፓርቲ ተወካዮችና የሚመከለታቸው  የፌደራል  ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ላይ በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ ሀገር የተመለሱ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውይይቱ የመነሻ ባቀረቡት ሓሳብ በቀጣይ የሚከናወነው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ምን መልክ ይኑረው በሚለው ላይ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ውይይትን በማካሄድ ጉዳዮች የሚፈቱበት መንገድ፣ ውይይቶች መቼ፣ እንዴት፣ በማን እና በምን ሓሳብ የሚሉትንም በዚህ ውይይት መዳሰስ እንዳለበት ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአጠቃላይ የዛሬው መድረክ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በይፋ መጀመሩን ያሳወቅንበትም  ነው ብለዋል ።

የውይይት  መድረኩን  ተከትሎም የብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የራሱን መርሃ ግብር እንደሚያወጣም  የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚካሄደው ምርጫ ከዚህ በፊት የሚነሳውን  ስሞታ ማስወገድ የሚያስችል መሆን አለበት ብለዋል ።

ከዚህ  ቀደም የነበሩ ውይይቶች ፍሬያማ  እንዳልነበሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ውይይቶቹ ከመነሻው ሲጀመሩ ተግባብቶ የጋራ ሓሳብ ይዞ ለመሄድ የሚደረጉ ባለመሆናቸው ፍሬ አልባ ሆነዋል ብለዋል ።

በአፍሪካ ቀደምት የመንግስት አስተዳደር የተከለችው ኢትዮጵያ በፖለቲካው ለአህጉሪቱ አርዓያ መሆን የሚያስችል በፖለቲካው ረገድ ባለመሥራቷ ገና የምትማር ሀገር ናት መሆኗን አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአንድ ሀገር የሚሰሩ እንደመሆናቸው መወያየት አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ያሸነፈው እና የተሸነፈው በጋራ ተነጋግሮ እንደሀገር ህልውናና መቀጠል በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ፓርቲዎች  የርዕዮተ ዓለምና የስትራቴጂ ልዩነታቸው  ከሀገር ህልውናናጥቅም እንዲሁም ከህዝብ ይሁንታ  በታች በማድረግ በዚያ ጥላ ስር በመሆን የጋራ ሀሳብ በነጻነት በመያዝ   መፎካከር እንደሚገባቸው  ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣም ከመጡ በኋላ በአገሪቷ መወሰድ ስለሚገባቸው ዘርፈ ብዙ ለውጦች  መካከል የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ቀዳሚው መሆኑን ደጋግመው ሲገልጹና ሲያረጋግጡ  እንደነበር ይታወሳል ።