የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የ59 አገራት ሚሲዮኖች፣ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችና የዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን ምደባ ይፋ አደረገ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በውጭ የሚገኙ 59 የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች፣ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችና የዋና መሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች ድልድልን ይፋ ማድረጉን አስታወቀ ።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገራት በሚገኙ  የ59 ሚሲዮኖችና በዋና መሥሪያ ቤቱ  በማገልገል  የሚገኙትን   ሠራተኞችን  በአዲስ  መልኩ  መመደቡን አስታውቋል ።

ሚኒስቴሩ  በተጨማሪም  የአዳዲስ  አምባሳደር  ሹመቶችን  በቅርቡ ይፋ  እንደሚያደርግም   ቃልአቀባዩ  አያይዘው  ገልጸዋል ።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ አዲሱ የሠራተኞች ምደባው የጎረቤት አገራትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችል ሁኔታና የሠራተኞችን የቆየ  ልምድና ችሎታ መሠረት በማድረግ የተከናወነ ነው ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ የሠራተኛ ድልድል ዋና ግብም ታሪክ የሚናገር ሳይሆን ታሪክ  የሚሠራ ዲፕሎማትን  መፍጠር እንደሆነም  ቃል አቀባዩ  በመግለጫቸው አብራርተዋል ።

በተለይም  በውጭ አገር የሚገኙ ዜጎች  በአገር  ጉዳይ  ላይ ያላቸውን ተሳትፎ  ማረጋገጥ  ሌላው የተቋሙ የአዲስ የሠራተኞች  ድልድል ዋነኛ ግብ  መሆኑን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል ።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተካሄደው አዲስ የዲፕሎማቶችም በአራት የትኩረት  መስኮች በሆኑት የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ  ማፍራት ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን  ማጠናከር  ፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችን የተሻለ ተሳትፎ  በማጠናከርና   የቆንስላ አገልግሎትን ይበልጥ  ተደራሽ  ማድረግን በሚያስችሉ አራት  ጉዳዮች ላይ እንደሚሠሩ ይጠበቃል ።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ወጥተው የቀሩ በሩቅ  ምስራቅና አፍሪካ  አገራት በሆኑት  በሳውዲአረቢያ ፣ ሊቢያ ፣ የመንና  ታንዛኒያ  የተሰደዱ  2ሺህ  ዜጎችን ለመመለስ  የተጀመረውን ጥረትም   አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ቃል አቀባዩ  በመግለጫው አመልክተዋል  ።

እስካሁንም ድረስ  በየመን  በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ  ከ200  የሚበልጡ ዜጎች   ከተለያዩ አካላት  ጋር በመተባባር  እንዲመሰሉ መደረጉንም ቃል አቀባዩ አያይዘው  ገልጸዋል