ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ለመላው አፍሪካ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው -ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ቲቦር ናጊ

በአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ለመላው አፍሪካ ምሳሌ መሆን የሚችልና  አሜሪካም በአድናቆት እንደምትመለከተው ገልጸዋል።

ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር ተናግረው የለውጡ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያመጡት ለውጥ ትልቅ ምስጋና የሚገባው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኤርትራና ሶማሊያን ጨምሮ ከቀጠናው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት ለውጥ አበርክቶ እንዳለው ያስተላለፉት መልዕክትና የጀመሩት ለውጥ አስደናቂ መሆኑንም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጠላት ሳይሆኑ፥ ተፎካካሪ ናቸው በሚል አብሮ መስራት መጀመራቸው ለአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ትልቅ ትምህርት ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የለውጥ ሂደት አስፈላጊ በሆነው መንገድ ሁሉ አሜሪካ ድጋፏን እንደምትቸርና ወቅታዊ ሁኔታውን ለዓለም በማስተገባት ጭምር የሚጠበቅባትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ቲቦር ናጊ አረጋግጠዋል።  

በተለይም የሰው ልጅ አዕምሮ ላይ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም የአሜሪካ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እና የስራ እድል እንዲፈጥሩ እናበረታታለን ብለዋል።

እኤአ ከ1999 እስከ 2002 በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቲቦር ናጊ በወቅቱ ኤርትራን ለመጎብኘት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ሁለቱ ሀገራት የነበሩበት ወቅታዊ ሁኔታ እንዳልፈቀደላቸው እና ያም እንደሚቆጫቸው ተናግረው አሁን ግን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ ለመጓዝ መዘጋጀታቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የአሜሪካ አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚያቀኑ ሲሆን፥ በዚያም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ አስታውቀዋል።

የጅቡቲ ቆይታቸውንም አጠናቀው ወደ ኤርትራ በማቅናት በአስመራና ዋሽንግተን መካክል ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንደሚመክሩም ነው የተገለጸው።

ኬንያ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ ሚኒስትሩ የአፍሪካ የመጨረሻ መዳረሻ መሆኗም ታውቋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)